ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሁሉም ሀገር የራሱ ብሔራዊ ጥቅም እና ፍላጎት እንዳለው ጠቅሰው፤ ብሔራዊ ጥቅም እና የብሔራዊ ደህንነት ስጋቶች ግን ባሉት መረዳት ልክ ይለያያሉ ብለዋል።
አክለውም ሁሉም ሀገር ዛሬ ብሔራዊ ጥቅሜ ነው ያለውን ነገር ሊያሰፋ ወይምሊያጠብ ይችላል፤ ዛሬ ስጋት የሆነበት ነገ ላይሆንበት ይችላል ሁሉም ነገር የሚሆነው ባለው እውቀት እና መረጃ ላይ ነው ብለዋል።
”የራሱ የብሔራዊ ጥቅም እና ብሔራዊ ደህንነት ስጋት የሌለው ሀገር የሚባል ነገር የለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፤ ”ኢትዮጵያ ኢ-ፍትሀዊ፣ ኢ-ርትአዊ እና የበደል መጨረሻው በደል የተፈፀመባት ሀገር ናት” ብለዋል።
እውነተኛ ፍትህ ካልተረጋገጠ ይህ በማንኛውም ሰአት ሊፈጠር ይችላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢ-ፍትሀዊ እና ኢ-ርትአዊ ውሳኔ ባለበት ሁኔታ የተሟላ ሰላም ሊፈጠር አይችልም ሲሉ ተናግረዋል።
አባይን በመገደባችን ማንንም አልጎዳንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግብፃውያን እና ሱዳናውያን ወንድሞቻችን ናቸው፡፡
ብንፈልግም ባንፈልግም ስልጣኔያችን የተቀራረበ እና የተመሳሰለ ነው የሚሻለን ከመባላት ይልቅ አብሮ መስራት ነው ብለዉ፤የምትታለብን ላም መኖ ነፍጎ ወተት መጠበቅ አግባብ አይደለም ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን፣ ሱዳናውያን እና ግብፃውያን አብረን ብንሰራ ታላቅ መሆን እንችላለን፤ ነገር ግን ”እኛ በህይወት እያለን ማንም በጉልበት ፍላጎቱን ሊጭንብን አይችልም ፤ እኛ ለዚህ አልተሰራንም የሚያዋጣን መስማማት ነው” በማለት 6ተኛው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ተኛ አመት የስራ ዘመን 2ተኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
ሀና ሰይፉ
ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም
