ለኢትዮጵያ ጥቅምና ብልፅግና ከጎኗ መቆም የማይሻ፣ ራሱን እንደ ማንጎ የሚቆጥር ግራዋ ነው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህን የተናገሩት በዛሬው የጥቅምት 18፣ 2018 ዓ.ም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ንግግራቸው ወቅት “ኢትዮጵያ ሲያምርባት አይኑ የሚቀላ፣ ሕዳሴ ሲያልቅ ከሰው ያጣላናል ለምን ያስፈልጋል? የሚል፣ የባህር በር ጥያቄ ሲነሳ የሚሸማቀቅና የሚያፍር፣ ደፈር ብሎ 130 ሚሊዮን ህዝብ ያስፈልገዋል ለማለት የሚተናነቀው፣ ለኢትዮጵያ ጥቅምና ብልፅግና ከጎኗ መቆም መድከም የማይሻ፣ ራሱን እንደ ማንጎ የሚቆጥር ግራዋ ነው” ብለዋል፡፡

“ራስህን በጠራህበት መንገድ ብቻ ሳይሆን በፍሬ ትታወቃለህ” ያሉት ዐቢይ፤ “ልክ እኛ እንደከተማ እና ገጠር ኮሪደር፣ ስንዴ እርሻ፣ አረንጓዴ አሻራ ባሉ ፍሬዎቻችን እንደምንታወቀው” ሲሉም አክለዋል፡፡

አናውቅም ካላችሁ ተመድን ጠይቁ፣ ተመድ በስንዴና በአረንጓዴ አሻራ ሸልሞናል በማለትም ጭምር፡፡

በተቃራኒው “ባንዳ” ሲሉ የጠሯቸውን አካላት ባይናገሩ እንኳ ተግባራቸው ከፍሬያቸው ያስታውቃል በማለት ወቅሰዋቸዋል፡፡

“ኢትዮጵያ ውስጥ የተገደበ ፓርቲ የለም፤ሰላማዊ ትግል ማድረግ ለሚፈልግ ሰው በሩ ክፍት ነው ያሉ ሲሆን፤ችግር የሆነው ሃሳብ መጥፋቱ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡

ሃሳብ መጥፋቱን ለማወቅ የእነዚህን ባንዳዎች ውሎ ማየት በቂ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ “ውሏቸውን ስታዩ ዛፍ በፍሬው እንደሚያስታውቀው ሁሉ እነሱም ያስታውቃሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ፓርቲ፣ ምርጫ፣ ህገ መንግስት፣ ወጣት፣ ተስፋ የሌለበት ሀገር ተለጥፎ ለኢትዮጵያ ተስፋ ሊያመጣ የሚችል ሰው የለም፤ ከማን ይማራል?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ማንነታቸውን በይፋ ያልገለጿቸውንና ‘እነርሱ’ ሲሉ የጠሯቸውን አካላት በማንሳትም “የእነርሱን ዴሞክራሲ ይማራሉ እንዳይባል መንግስት አይታወቅ፣ ካቢኔ፣ ፓርቲ፣ ምርጫ አይታወቅ፡፡ ምርጫ የሌለበት ተለጥፎ ስለምርጫ መጠየቅ አይገርምም?” በማለት ለምክር ቤቱ ተናግረዋል፡፡

የሚያሳዝነው ነገር ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የጠቀሱት ጉዳይ የትላንት እና የዛሬ ፓርቲዎች ተመሳሳይ ፋሽን ሲሉ የጠቀሱት አካሄድን ነው፡፡

“ኢትዮጵያ ውስጥ ትላንት ገንጣይ አስገንጣይ ወይም ነፃ አውጭ የሚባለው ስብስብ ፓርቲ ለመባል የመጀመሪያው ፕሮግራሙ ላይ የሚፅፈው ‘የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ መሆኑን እቀበላለሁ’ በማለት ነበር” እንደምሳሌ ሕወሃትንና ኦነግን የጠቀሱት፡፡

የዛሬዎቹ ደግሞ የባህር በር ጉዳይ እኛን አይመለከተንም ካላሉ ይታገሉ አይመስላቸውም፤ ፋሽኑ አንድ ነው መማር ግን አልቻሉም በማለት ነው የተናገሩት፡፡

አዲስአለም አበበ

ጥቅምት 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *