ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከተማዋን በተቆጣጠረ በጥቂት ቀናት ዉስጥ በሳዑዲ የእናቶች እና ህጻናት ሆስፒታል ላይ ባደረሰዉ ጥቃት 4መቶ60 ንጹሃንን መግደሉን የዓለም ጤና ድርጅት ነዉ ያስታወቀዉ፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኃኖም፤ የደረሰዉን ዘግናኝ ጥቃት ስንሰማ በእጅጉ ደንግጠናል ብለዋል፡፡
ቀደም ብሎ የሱዳን ዶክተሮች ኔትዎርክ ፤ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አባላት በሆስፒታሉ የነበሩ ታካሚዎችን፣ አስታማሚዎቻቸዉን እንዲሁም በሆስፒታሉ የተገኙ ሁሉንም ንጹሃን ዜጎች በጭካኔ ገድለዋል ሲል አስታዉቆ ነበር፡፡
የሟቾችን ቁጥር ይፋ ባያደርግም በከተማዋ የሚገኙ የህክምና ተቋማት ለግድያ የተዘጋጁ ቤቶች ሆነዋል ሲል ነበር ሁኔታዉን የገለጸዉ፡፡
በተጨማሪም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ 6 የሆስፒታሉን ሰራተኞች አፍኖ መዉሰዱን እና እነሱን ለማስለቀቅም ከ1መቶ50 ሺህ ዶላር የበለጠ ገንዘብ እየጠየቀ መሆኑን ተናግሯል፡፡
የኤል-ፋሸር ከተማ እሁድ ዕለት በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቁጥጥር ስር እስክትገባ ድረስ በዳርፉር ክልል በወታደራዊ ኃይሉ የተያዘች የመጨረሻዋ ከተማ ነበረች እንደ ቢቢሲ ዘገባ፡፡
እስከዳር ግርማ
ጥቅምት 20/2018 ዓ.ም
