አዉሎንፋስ ካልማጊ ፊሊፒንስ እና ቬትናም ውስጥ በትንሹ 1መቶ93 ሰዎችን ከገደለ በኋላ ወደ ካምቦዲያ እያመራ ነው።

እንደ መረጃዎች ከሆነ ታይፎን ካልማጊ ፊሊፒንስ ውስጥ 1መቶ88 ሰዎችን ቬትናም ውስጥ ደግሞ የ5 ሰዎችን ህይወት ነጥቋል፡፡

አውሎ ነፋሱ በመካከለኛው ቬትናም በሰዓት እስከ 1መቶ49 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት ካለፈ በኋላ አሁን ወደ ምዕራብ ካምቦዲያ እና ላኦስ እያመራ ነው ተብሏል።

የቬትናም ባለሥልጣናት ዝቅተኛ ቦታዎች ላይ የጎርፍ መጥለቅለቅ ሊኖር እንደሚችል ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡

በማዕከላዊ ቬትናም ባለፈው ሳምንት በከፍተኛ ዝናብ በደረሰ የጎርፍ አደጋ የ50 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ተመሳሳይ አውሎ ነፋስ በፊሊፒንስ የተለያዩ ክፍሎች ላይ ውድመት አድርሷል፡፡

አንዳንድ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሰፈሮች በከፍተኛ ፍጥነት በሚመጣዉ ጎርፍ ሙሉ በሙሉ ወድመዋል ነዉ የተባለዉ።

ዛሬ የተገለጸዉ የሟቾች ቁጥር ትናንት ከነበረዉ 1መቶ14 ሰዎች ከፍ ያለ ሲሆን፤ ሌላ 1መቶ35 ሰዎች እንደጠፉ ተዘግቧል፡፡

የፊሊፒንስ መንግሥት በፓሲፊክ ውቅያኖስ ውስጥ እየተፈጠረ ላለው ሌላ አውሎ ነፋስ እየተዘጋጀ በመሆኑ በመላ አገሪቱ የአደጋ ጊዜ አዋጅ ታዉጇል፡፡

አዉሎንፋሱ ከመምጣቱ በፊት የቬትናም ጦር ኃይል ሐሙስ ዕለት ከ2መቶ60 ሺህ በላይ ወታደሮችን እና የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን፣ከ6 ሺህ7መቶ በላይ ተሽከርካሪዎች እና ስድስት አውሮፕላኖችን አሰማርቷል።

በአገሪቱ ውስጥ አንዳንድ አውሮፕላን ማረፊያዎች እና አውራ ጎዳናዎች ተዘግተዋል የተባለ ሲሆን፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል እንደ ቢቢሲ ዘገባ።

ሊዲያ ደሳለኝ

ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *