የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) በአሜሪካ የቀረበውን የሰብአዊነት ተኩስ አቁም ስምምነት መቀበሉን ሐሙስ ዕለት አስታውቋል።
የሱዳን ወታደራዊ ጦር ግን እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። አርኤስኤፍ መግለጫ ያወጣው በምዕራብ ዳርፉር የሚገኘውን የኤል-ፋሸር ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው።
በከተማዋ ዙሪያ ለ18 ወራት ከበባ አድርጓል። ከበባው እንዲቆም የተባበሩት መንግሥታትን ተደጋጋሚ ጥሪ ችላ በማለቱ ለመሸሽ የማይችሉ ነዋሪዎችን ለረሃብ አጋልጧል።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው ዓለም አቀፉ የረሃብ ክትትል ቡድን በከተማው ውስጥ የረሃብ ሁኔታዎች መከሰታቸውን አረጋግጧል።
አርኤስኤፍ በእግረኛ ወታደሮቹ የጅምላ ግድያ ሪፖርቶች ምክንያት ዓለም አቀፍ ተቃውሞ እያጋጠመው ቢሆንም ቡድኑ ክሱን አስተባብሏል። “ጥሰቶች” በግለሰቦች ደረጃ የተፈጸሙ መሆናቸውን አምኖ አንዳንዶቹን አስሯል።
እአአ በ2023 ነበር በሱዳን ጦር እና በአርኤስኤፍ መካከል የእርስ በእርስ ጦርነት የተጀመረው። ሁለቱም ወገኖች በጦርነቱ ወቅት የተለያዩ የተኩስ አቁም ሐሳቦችን ቢቀበሉም አንዳቸውንም አልተገበሩም።
በመስከረም ወር አሜሪካ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከግብጽ ጋር በመሆን ለሦስት ወራት የሚቆይ የሰብአዊ ስምምነት፣ ቀጥሎም ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም እና ወደ ሲቪል አገዛዝ ሽግግር የሚሄድ ሐሳብ አቅርበዋል።
የአርኤስኤፍ መግለጫ እንዳመለከተው “የጦርነቱን አስከፊ ሰብአዊ ውጤቶች ለመፍታት” እና “አስቸኳይ የእርዳታ አቅርቦት” እንዲደርስ ለመፍቀድ አራቱ አገራት ባቀረቡት የተኩስ አቁም ሐሳብ መስማማቱን ገልጿል ሲል ቢቢሲ ዘግቧል።
ጥቅምት 28/2018 ዓ.ም
