የአሜሪካ ሴኔት ለ40 ቀናት የቆየዉን የፌደራል ሰራተኞችን ከስራ ያስወጣዉን፣ የምግብ እርዳታ እንዲዘገይ እና የአየር ጉዞን ያስቀረዉን መዘጋት ለማቆም ያለመ ረቂቅ ህግ አቅርቧል፡፡
ሴናተሮች የፌደራል መንግስትን እስከ ጥር 30 የሚደጉም እና የሶስት ዓመት ሙሉ የድጋፍ ህግጋትን የሚያካትት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ ረቂቅ ህግ አቅርበዋል።
ሴኔቱ በመጨረሻ የተሻሻለውን ረቂቅ ህግ ቢያጸድቅ እንኳን የግድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊርማ መላክ አለበት፤ ይህም ሂደት ብዙ ቀናት ሊወስድ ይችላል።
ከጥቂት ዴሞክራቶች ጋር በተደረገ ስምምነት ሪፐብሊካኖች ድጎማዎችን ለማራዘም በታህሳስ ወር ድምጽ ለመስጠት ተስማምተዋል።
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አሜሪካውያንን የግል የጤና መድህን ለመክፈል የሚያግዙት እና በዓመቱ መጨረሻ የሚያበቁት ድጎማዎች ዴሞክራቶች ቅድሚያ ሰጥተዉ ሲከራከሩባቸዉ የቆዩ ጉዳዮች ናቸዉ፡፡
ረቂቅ ህጉ የፌደራል ኤጀንሲዎች ሰራተኞችን እስከ ጥር 30 ከስራ እንዳያባርሩ የሚከለክል ሲሆን፤ ይህም ለፌደራል ሰራተኛ ማህበራት እና አጋሮቻቸው ትልቅ ድል ነው ተብሏል።
እንደ ፌደራል መዛግብት ከሆነ ትራምፕ ሁለተኛ የስልጣን ዘመናቸውን ሲጀምሩ 2.2 ሚሊየን ሲቪሎች ለፌደራል መንግስት ሲሰሩ ነበር፡፡
በትራምፕ ሰራተኞችን የመቀነስ ዕቅድ ምክንያት ቢያንስ 3 መቶ ሺህ ሰራተኞች በዚህ ዓመት መጨረሻ ከመንግስት እንደሚለቁ ይጠበቃል ሲል የዘገበዉ ሮይተርስ ነዉ።
ረቂቅ ህጉ 60 ለ 40 በሆነ ድምጽ ፀድቋል፡፡
ሀና ሰይፉ
ህዳር 01/2018 ዓ.ም
