በክልሉ የአካል ጉዳተኞች መጠን 28 በመቶ ደርሷል ተብሏል።
በተደረጉ የተለያዩ ጥናቶች በክልሉ ከፍተኛ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር መኖሩ ተገልጿል።
ይህንን ምክንያት በማድረግ የዘንድሮው የዓለም የአካል ጉዳተኞች ቀን በትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀሌ ህዳር 24 ይከበራል።
ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በቂ ውይይት መደረጉን የገለፁት የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አባይነህ ጉጆ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ በዓሉን በሰላማዊ መንገድ ለማክበር ከክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር በቂ እና አስተማማኝ ማረጋገጫ አግኝተናል ብለዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ድኤታ ሁሪያ አሊም ይህንን ጉዳይ ማረጋገጫ ሰጥተዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ ዝግጅቱን ጨርሶ እየጠበቀን ነው ያሉ ሲሆን፥ እኛም የምንሄደው በዓል ለማክበር እንጂ ሌላ አላማ ይዘን አይደለም ብለዋል።
በትግራይ ክልል ብቻ ሳይሆን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙትን የአካል ጉዳተኞች ቁጥር ለማወቅ የህዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ምላሽ ይሰጠናል ሲሉ ሚኒስትር ድኤታዋ ተናግረዋል።
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከህንድ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በአፋር ክልል ለ2መቶ60 ፥ በትግራይ ክልል ደግሞ ለ1መቶ77 አካል ጉዳተኞች የአካል ተሀድሶ አገልግሎት መስጠቱንም ገልፀዋል።
ከቀረጥና ታክስ ነፃ ተሽከርካሪዎች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ከ5 ሺህ በላይ የሚሆኑ የአካል ጉዳተኞች ተጠቃሚ መሆናቸውንም አንስተዋል።
ዓለምአቀፍ የአካል ጉዳተኞች ቀን በዓለም ለ34ኛ በአገራችን ደግሞ ለ33ኛ ጊዜ ህዳር 24 ይከበራል።
በዓለምአቀፍ ደረጃ የሚከበረው ይህ ዕለት” አካል ጉዳተኞችን የሚያካትት ማህበረሰብ መገንባት ለተሻለ ማህበራዊ ዕድገት” በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
እስከዳር ግርማ
ህዳር 19/2018 ዓ.ም
