የጎልጎታ ባለይዞታዎች የስድስት ሃገራት አብያተ ክርስትያናት ናቸዉ። ከስድስቱ መካከል አንደኛዉ እኛ ነን። የጎልጎታ አባል የጎልጎታ ባለይዞታዎች ነን ይላሉ የገዳማቱ የሒሳብ ክፍል ሐላፊ መላከሰሌም አባ ገ/ኪዳን፡፡
ከስድስቱ መካከል ሦስቱ ታላላቆች ግሪክ፤ ላቲን እና አርመን ሲሆኑ፥ መለስተኛ አብያተ ክርስትያናት ተብለዉ የሚመደቡት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ- ክርስትያን ፤ የግብጽና የሶርያ ናቸዉ። የጎልጎታ ቀራንዮ በእነዚህ በስድስቱ የተያዘ ነዉ።
ገዳሙ ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ጀምሮ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን ርስት ሆኖ ሲገለገሉበት መቆየታቸው ይነገራል ፡፡ይሁን እንጂ አሁንም ድረስ ይህ ጥንታዊ ፤ ታሪካዊ ስፍራ በሌሎች ሊነጠቅ የሚችልበት ሆኔታ እንዳለ ስጋታቸውን ይናገራሉ እኚህ አባት ፡፡
በእስራኤል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተስፋዬ ይታይህ በዴር ሱልጣን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ጥረት ያላደረገ ያልደከመ እንደሌለ ይናገራሉ፡፡
በቅርቡ እንኳን የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር )፥ በእስራኤል በነበራቸው ቆይታ ስፍራው ድረስ በመሄድ ከአባቶች ጋር መመከራቸውን እና ከእስራኤሉ አቻቸው ጋርም በጉዳዩ ላይ መምከራቸውን ተናገረዋል፡፡
በስፍራው ያሉ መነኮሳት ያሉባቸውን ችግሮችም ለመቅርፍ ሰፊ ጥረት የተደረገ ቢሆንም 2መቶ አመታት ሲንከባለል የቆየ በመሆኑ በሚፈለገው ልክ ምላሽ ማግኘት እንደልተቻለ ገልጸዋል፡፡
በእስራኤል (ባለበት ይቆይ የሚባል ህግ አለ በጎለጎታ ያሉት የኢትዮጵያ ቤክርስቲያናት (መድኃኔአለም እና ሚካኤል ) እየተገለገለችባቸው ትገኛለች ፡፡ግብጾችም ስፍራውን አልወሰዱም እኛም አገልግሎቱን አላቋረጥንም ፡፡መነኮሳቱ ያሉባቸውን የመብራት ፤የውሃ የማዘጋጃ ቤት አገልግሎቶችን ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
ከጥቁር ሕዝብ መካከል በእስራኤል ይዞታ ያላት ኢትዮጵያ መሆኗን የሚመሰክሩት በኢትዮጵያ የእስራኤል አምባሳደር አቭራም ንጉሤ ፥ይህ ይዞታ በጎልጎታ ተራራ ላይ ብቻ ሳይሆን በቀድሞ ጊዜ ነገሥታቱ እና መኳንንቱ የሰሩት ብዙ ሕንፃና ንብረት እንዳለ አንስተው፤የእስራኤል መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ለቤተክርስቲያናቱ ድጋፍ እና ጥገና እያደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡
የእስራኤል ምክር ቤት አባል ጸጋ ፋንታሁን (ዶ/ር)በበኩላቸው ፥በእስራኤል በኩል ችግሩን ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ቢሆንም የሚመለከታቸው አባቶችን በሰአቱ ማግኘት ባለመቻላችን ችግሮ መቆየቱን አንስተዋል፡፡
የርስቱ ባለቤት ነኝ የምትለው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ጉዳይ ለመፍታት አንድም ጊዜ ጫና አድርጋ አታውቅም ተብላ ትወቀሳለች።
ርስቱ በመካከለኛው ምሥራቅ የኢትዮጵያን መንግሥት የሚወክል ሀብት ሆኖ ሳለ ይህንን ሀብት እንደሀገራዊ ሀብት ለማስከበር መንግሥትም ጠንከር ያለ ጫና ሊያደርግ ይገባዋል ተብሏል ።
ያይኔ አበባ ሻምበል
ህዳር 19/2018 ዓ.ም
