የዉሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ኘሮጀክቱ በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ላይ የተመረጡ ሁለት ቦታዎች ለተግባራዊነቱ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር እየተደረገ እንደሆነ ገልፆል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ደበበ ደፈርሶ ፕሮጀክቱ የመረጃና የውሃ አጠቃቀም ስርዓትን ፣የኢነርጂ አቅርቦትን፣ የበፈር ዞን ፣ የአካባቢ ጥበቃ እና የአፈርና ውሃ እቀባ ስራዎችን በማስተሳሰር ተግባራዊ እንደሚደረግ ገልፀዋል።
በቅድመ ዝግጅት ስራዎች ጥናት በማካሄድና መረጃ በመሠብሰብ እንዲሁም ሌሎች ምቹ ሁኔታዎችን በማስተካከል ወደ ትግበራ ለመግባት የሚያስችል ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ይገኛል ተብሏል።
አርብቶ አደርና ከፊል አርብቶ አደር አካባቢዎች ላይ ለውጥን የመቋቋም አቅም እንዲፈጠር እና የማህበረሰቡ የኑሮ ደረጃ እንዲሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነዉ ተብሏል።
የባዘርኔት ፕሮጀክት በጣሊያን ትብብር የ31.5 ሚሊየን ዩሮ የገንዘብ ድጋፍ በአዋሽ ፣ ደናክልና ዋቢ ሸበሌ ተፋሰሶች የሚተገበር ነዉ።
በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ ሊለሙ በተመረጡ ሁለቱ ንኡስ ተፋሰሶች ላይ ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ ለቀጣይ ሶስት አመታት ተግባራዊ የሚደረግ እንደሆነ ሰምተናል።
በዋቢ ሸበሌ ተፋሰስ በምስራቅ ሀረርጌ በባቢሌ ወረዳ የኢፋዲን ንኡስ ተፋሰስ እንዲሁም በሱማሌ ክልል ቀላፎ ወረዳ አልጎሪስ ንዑስ ተፋሰስ ላይ የተቀናጀ የውሃ ሀብት አስተዳደር ስራዎች ይተገበራሉ ተብሏል።
ልኡል ወልዴ
ህዳር 23/2018 ዓ.ም
