አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል የተባለ የብድር አገልግሎት ይፋ ተደረገ

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አነስተኛ ይዞታ ያላቸውን አርሶ አደሮችን እና አርብቶ አደሮችን ተጠቃሚ ያደርጋል ያለውን የብድር አገልግሎት ይፋ አድርጓል፡፡

ባንኩ በዛሬው ዕለት ይፋ ያደረገው የግብርና ብድር ቀደም ሲል በግብርና ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ከሚሰጠው ብድር በተለየ፣ ለግለሰብና በቡድን የተደራጁ አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ተብሏል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎቶች ኤክስኪውቲቭ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በመርሐ ግብሩ ላይ ሲናገሩ፣ ይፋ የተደረገው የብድር አገልግሎት ለሰብል ምርት፣ ለእንስሳት እርባታ፣ ለወተት እና የወተት ተዋፅኦ ምርት፣ ለአትክልት፣ ፍራፍሬ እና አበባ ልማት፣ እንዲሁም ለግብርና መሳሪያዎች ግዥ የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

አቶ ኤፍሬም አክለውም ባንኩ ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለግብርና ፕሮጀክቶች በአነስተኛ የወለድ መጠን የብድርና ሌሎች አገልግሎቶችን እየሰጠ ቆይቷል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴዔታ መለስ መኮንን (ዶ/ር)፣ የብሔራዊ ባንክ ተወካይ ወ/ሮ ወይንሸት ዘበርጋ እና ሌሎችም የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

አዲስዓለም አበበ

ታህሳስ 09/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *