የኤም23 አማፂ ቡድን በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከምትገኘውና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ካላት የኡቪራ ከተማ መውጣቱን አስታዉቋል።
ይህ እርምጃ የተወሰደው በኤም23 እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር መካከል ያለውን ግጭት ለመፍታት በሚጥሩት የአሜሪካ አደራዳሪዎች ጥያቄ እንደሆነ ተዘግቧል።
የኤም23 አማፂ ቡድን ኃይሎቹን በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከምትገኘው ኡቪራ ከተማ እንዲያወጣ ከአሜሪካ አደራዳሪዎች ከአንድ ቀን በፊት የቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉን አስታውቋል።
ኤም23 በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎችን ለሞት እና ለመፈናቀል በዳረገ አሰቃቂ ግጭት ውስጥ በመሳተፍ ባለፈው አንድ ዓመት በአካባቢው ከኮንጎ ጦር ጋር ሲዋጋ ቆይቷል።
ኤም23ን ትደግፋለች ተብላ የምትከሰሰው ሩዋንዳ እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ መሪዎች፤በአሜሪካ አደራዳሪነት የተዘጋጀውን የሰላም ስምምነት በዋሽንግተን ቢፈራረሙም፤የኤም23 አማፂያን በድርድሩ ውስጥ አልተካተቱም ነበር።
በዚህም ምክንያት የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ ከጥቂት ቀናት በኋላ በብሩንዲ እና ሩዋንዳ ድንበር አቅራቢያ የምትገኘውን የኡቪራ ከተማን ተቆጣጥረው ነበር።
ኤም23 ከከተማዋ የሚወጣው ‹‹ለሰላም ሲባል›› እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፤ወታደሮቹም በገዛ ፈቃዳቸው ከተማዋን መልቀቅ እንደጀመሩ ሪፖርቶች አረጋግጠዋል።
ከስፋራዉ ጠቅልሎ የመዉጣት ሂደት ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል እንደ አፍሪካ ኒዉስ ዘገባ።
እስከዳር ግርማ
ታህሳስ 09/2018 ዓ.ም
