ለመደበኛ ሰራተኞች የሚሰጠው ማህበራዊ የጤና መድህን አገልግሎት ወደ ትግበራ ገብቶ፤ እስካሁን ከ5መቶ ሺህ በላይ ሰራተኞች መመዝገባቸው ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ ደግሞ ከ63 ሚሊየን በላይ ዜጎች የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡
የኢትዮጵያ ጤና መድህን አገልግሎት በአሁኑ ወቅት ከ63 ሚሊየን በላይ ዜጎችን የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አስታዉቋል፡፡
የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ወርቁ ፤ ተቋሙ ቀደም ሲል ከነበረው ኤጀንሲነት ወደ አገልግሎት ሰጪነት ከተቀየረ በኋላ አደረጃጀቱን በማስፋት 24 ቅርንጫፎችን በመክፈት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ሰዓት አገልግሎቱ በሀገሪቱ ከሚገኙ ወረዳዎች 80 በመቶ ያህሉን የሸፈነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከ4 ሺህ 3መቶ በላይ ጤና ጣቢያዎች እና በርካታ ሆስፒታሎች የአገልግሎቱ አጋር በመሆን እየሰሩ መሆኑን ነዉ ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ለመደበኛ ሰራተኞች የሚሰጠው ማህበራዊ የጤና መድህን አገልግሎት ወደ ትግበራ መግባቱን ጠቅሰው፤እስካሁን ከ5መቶ ሺህ በላይ ሰራተኞች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡
በዚህም መሰረት ሰራተኛው 3 በመቶ እንዲሁም አሰሪው 3 በመቶ በማዋጣት የህክምና ሽፋን የሚያገኙበት አሰራር ተዘርግቷል፡፡
የመድሃኒት አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ከኢትዮጵያ መድሃኒት አቅራቢ አገልግሎት ጋር የውል ስምምነት ተደርጎ በቅድመ ክፍያ እየተሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡
አሰራሩን ለማዘመን እና ብክነትን ለመቀነስ የዲጂታል መታወቂያ እና የመረጃ አያያዝ ስርዓት እየተዘረጋ መሆኑንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል፡፡
ሊዲያ ደሳለኝ
ታህሳስ 10/2018 ዓ.ም
