የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ (ኢጃት) የታኅሣሥን ወር የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ “የአእላፋት ሳምንት” የተሰኘ ታላቅ ዐውደ ርዕይና የጃን ፎረም መድረክ ሊያካሂድ መሆኑን አስታወቀ ።
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ መሠረት፣ ዝግጅቱ ከታኅሣሥ 16 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ 23 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በግዮን ሆቴል ቅጥር ጊቢ ውስጥ ይካሄዳል ።
አዘጋጆቹ እንዳሉት የዚህ ዝግጅት ዋና ዓላማዎች የማኅበሩን ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ማስተዋወቅ፣
የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ገዳማትና አድባራት ሥራዎቻቸውን የሚያቀርቡበት መድረክ መፍጠር፣ ሊቃውንትና ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎችን የሚያቀርቡበት የዐውደ ጥናት መድረክ ማዘጋጀት ናቸው ።
በዚሁ መርሐግብር ላይ የቅዱስ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ 600ኛ ዓመት የሚዘከር ሲሆን፣ ለገዳሙ የሚሆን የገና መባዕ ማሰባሰቢያ መድረክም ይኖራል ተብሏል ።
በተጨማሪም የዲያቆን ምሕረት “Defending the ancient faith” የተሰኘ መጽሐፍ ምርቃትና የነገረ መለኮት ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች ለታዳሚው ይቀርባሉ ።
ለሕጻናትም ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ “ጃን አግናጥዮስ” በተሰኘው ክፍል አማካኝነት ከታኅሣሥ 17 ቀን ጀምሮ የተለያዩ ሃይማኖታዊ ጨዋታዎችና ኤግዚቢሽኖች ተዘጋጅተዋል ።
ማኅበሩ አክሎም እንደገለጸው፣ 3ኛው የአእላፋት ዝማሬ መርሐግብር ታኅሣሥ 28 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ እና በድሬደዋ ለገሀር አደባባይ ከቀኑ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ በድምቀት ይካሄዳል ።
ከዚህም በተጨማሪ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ የተለያዩ አድባራትና ማኅበራት ይህንን ዝማሬ በየአካባቢያቸው እንዲያዘጋጁ የልምድ ልውውጥ መደረጉ ታውቋል ።
መላው ምዕመናን በግዮን ሆቴል በሚከናወነው ዝግጅት ላይ በ300 ብር የመግቢያ ክፍያ እንዲታደሙ ጥሪ ቀርቧል ።
ልኡል ወልዴ
ታህሳስ 10/2018 ዓ.ም
