በኢትዮጵያ ወጣት የሶፍትዌር መሃንዲሶች የበለፀገውና የማህበራዊ ትስስርን ከዘመናዊ የንግድ ስርዓት (e-commerce) ጋር ያዋሃደው “ዳንቴል” የተሰኘ የሞባይል መተግበሪያ ስራ ጀምረዋል ።
ባለፉት ሶስት ዓመታት በምርምርና ዝግጅት ላይ የቆየው ዳንቴል ሶፍትዌር ኃ.የተ.የግ.ማህበር፣ በተለይ ወጣቶች እና ሴቶች ያለ ምንም መነሻ ካፒታል በዲጂታል ንግድ እንዲሳተፉ የሚያስችል ምቹ መድረክ መፍጠሩን የድርጅቱ መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ፊሊጶስ ማርሳይ ገልፀዋል።
እንደ አቶ ፊሊጶስ ማብራሪያ፣ “ዳንቴል” ተራ የገበያ መተግበሪያ ብቻ ሳይሆን በሰው ሰራሽ አስተዝህሮ (AI) የታገዘ የንግድ አማካሪም ጭምር ነው።
ተጠቃሚዎች በመተግበሪያው ላይ የሚገኙ ምርቶችን በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው እንደ ቴሌግራም፣ ፌስቡክና ቲክቶክ በማጋራትና ሽያጭ እንዲከናወን በማድረግ የኮሚሽን ተጠቃሚ እንዲሆኑ እድል ይፈጥራል።
ይህ አሰራር በተለይ የስራ ልምድ ያላቸው ነገር ግን ወደ ስራው ዓለም ለመግባት በካፒታል እጥረት ለተቸገሩ ወጣቶች እንደ ትልቅ ድልድይ ያገለግላል ተብሏል።
መተግበሪያው ተጠቃሚዎች የትኛውን ምርት፣ በምን አይነት የገበያ ሁኔታ እና በምን ያህል ካፒታል መጀመር እንዳለባቸው የሚያማክር የራሱ የሆነ የAI ስርዓት አለው።
ይህም አምራቾችና ነጋዴዎች የገበያ ፍላጎትን ተረድተው ምርታቸውን በብቃት እንዲያቀርቡ ይረዳቸዋል።
“ዓላማችን ማህበረሰብን ማብቃትና ሽያጭን ማሳደግ ነው” የሚለው የድርጅቱ መሪ ቃል፣ በቴክኖሎጂ ታግዞ ወደ ተግባር መለወጡን ድርጅቱ ገልጿል።
ዳንቴል ከአምራቾች እስከ ሸማቾች ያለውን ሰንሰለት ለማሳለጥ ከኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ጋር በቅንጅት እየሰራ ይገኛል።
ይህም ተጠቃሚዎች የሚያዝዟቸው ምርቶች ባሉበት ቦታ ሆነው እንዲደርሷቸውና የት ደረጃ ላይ እንዳሉ እንዲከታተሉ ያስችላቸዋል።
በተጨማሪም ድርጅቱ የደንበኞችን እምነት ለመጠበቅ “ምርቱ ካልተመቸ የመመለስ መብት” (Return Policy) ከአቅራቢዎች ጋር ስምምነት ላይ ደርሶ ተግባራዊ እያደረገ መሆኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አመልክቷል።
ልኡል ወልዴ
ታህሳስ 17/2018 ዓ.ም
