የቱርክ ፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ከሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ጋር በሱዳን እየተባባሰ የመጣውን የእርስ በርስ ጦርነትና ሰብአዊ ቀውስ በሚመለከት በቱርክ መዲና አንካራ ከፍተኛ ውይይት አደረጉ።
በተካሄደው በዚህ ስብሰባ ላይ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በሱዳን ያለው ግጭት በዓለም ላይ አስከፊ ከሚባሉ ሰብአዊ ቀውሶች አንዱን ማስከተሉን ገልጸዋል።
እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ከሆነ፣ ከሚያዝያ 2015 ዓ.ም. (April 2023) ጀምሮ የተቀሰቀሰው ይህ ጦርነት እስካሁን 13 ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል።
ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን በተለይም በኤል-ፋሸር አካባቢ እየተፈጸሙ ያሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችንና የሰላማዊ ዜጎችን ስቃይ በጥብቅ አውግዘዋል።
ቱርክ ለሱዳን የምታደርገውን ሰብአዊ እርዳታ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ቃል ገብተዋል።
የቱርኩ መሪ በሱዳን በአፋጣኝ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ጥሪ አቅርበዋል። ቱርክ የሱዳንን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት እንደምትደግፍም በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ከጦርነቱ ባለፈ ሁለቱ ሀገራት በንግድ፣ በግብርና፣ በማዕድን እና በመከላከያ ኢንዱስትሪ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማሳደግ ተስማምተዋል።
የሱዳን ጦር እና የፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይሎች (RSF) የሚያካሂዱት ይህ ጦርነት አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ የቀጠለ ሲሆን፣ የቱርክ መንግሥት ለቀውሱ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲገኝ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቱን እንደሚቀጥል ገልጿል ሲል አፍሪካ ኒውስ ዘግቧል።
ልዑል ወልዴ
ታህሳስ 17/2018 ዓ.ም
