የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማህበር አቅም ለሌላቸው ወጣቶች የክህሎት ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እያሰማራ መሆኑን ገለጸ

የኢትዮጵያ ወጣት ወንዶች ክርስቲያን ማህበር በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ሲያሰለጥናቸው የቆዩ 1መቶ21 ወጣቶችን ያስመረቀ ሲሆን፤ ማህበሩ ስልጠናውን ያለምንም ክፍያ (በነጻ) በመስጠት ወጣቶችን ለስራ እያዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል።

ማህበሩ በተለይም በክረምት ወራት ወጣቶችን በስፋት የሚያሳትፉ ስልጠናዎችን እያከናወነ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል ወደ አረብ ሀገራት ለስራ ለሚሄዱ ሴቶች መሰረታዊ የአረብኛ ቋንቋ ስልጠና፣ እንዲሁም ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ለስኮላርሺፕ ፈላጊዎች የፈረንሳይኛ ቋንቋ ስልጠናዎችን በነጻ ይሰጣል።

ከቋንቋ ስልጠና ባለፈ የወቅቱን የገበያ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ እንደ ኮዲንግ (Coding)፣ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ (AI)፣ ማሽን ለርኒንግ እና የሞባይል መተግበሪያ ልማት (App Development) ስልጠናዎች በክረምት ፕሮግራሞች ውስጥ ተካተዋል።

በተጨማሪም በግራፊክ ዲዛይን፣ በፋሽን፣ በምግብ ዝግጅት እና በውበት አጠባበቅ ዘርፎች ወጣቶች ስልጠና ወስደው ራሳቸውን እንዲችሉ እየተደረገ ይገኛል።

የወ.ወ. ከ. ማ አዲስ አበባ ቅርንጫፍ ማኔጀር አቶ ተስፋጽዮን እንደገለጹት፤ ብዙ ወጣቶች የስልጠና ክፍያ መክፈል ባለመቻላቸው የተነሳ ተስፋ ሲቆርጡ ይታያሉ።

ዋይኤምሲኤ ይህንን ክፍተት ለመሙላት አቅም ለሌላቸው ወጣቶች በነፃ እንዲሰለጥኑ ዕድሉን አመቻችቷል ብለዋል።

ማህበሩ ስሙ “የወጣት ወንዶች” ቢልም፣ አገልግሎቱ ግን ለሁሉም ወጣቶች ክፍት መሆኑንና በአሁኑ ወቅት በስልጠናዎቹ ላይ የሚሳተፉት ሴቶች ቁጥር ብልጫ እንዳለውም ተገልጿል።

ለዓለም አሰፋ

ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *