ዶናልድ ትራምፕ እና ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በፍሎሪዳ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ያካሄዱትን ውይይት ተከትሎ መሻሻሎች መታየታቸውን ቢናገሩም፣ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ግን የግዛት ጉዳይ አሁንም “አልተፈታም” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እሳቸውና ዘለንስኪ “ብዙ ነገሮችን እንደተወያዩ” ከሁለትዩሽ ውይይቱ በኋላ ተናግረዋል።
ትራምፕ እሳቸውና ዘለንስኪ ከአውሮፓ መሪዎች ጋርም መነጋገራቸውን ገልጸዋል።
የአሜሪካም ሆነ የዩክሬን ፕሬዚዳንቶች ውይይቱን “በጣም ጥሩ” ሲሉ ቢገልጹትም፣ ትራምፕ “አንድ ወይም ሁለት በጣም አወዛጋቢ ጉዳዮች” አሁንም ድረስ ሳይፈቱ ቀርተዋል፤ በተለይም በግዛት ጉዳይ ብለዋል።
ዜሌንስኪ በማር አ ላጎ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ከባለ 20 ነጥብ የሰላም ዕቅዱ መካከል “90 በመቶ” ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ሲገልጹ፣ ትራምፕ ደግሞ ለዩክሬን የተሰጠው የደህንነት ዋስትና “ወደ 95 በመቶ የሚጠጋው” ተጠናቋል ብለዋል።
ዜሌንስኪ የአሜሪካ እና የዩክሬን ልዑካን በሚቀጥለው ሳምንት ለአራት ዓመታት ያህል የቀጠለውን ጦርነት ለማስቆም ያለሙ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ እንደሚገናኙ ተናግረዋል።
ዜሌንስኪ በቴሌግራም የመልዕክት መላላኪያ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት “በሁሉም ጉዳዮች ላይ ጉልህ ውይይት አድርገናል፤ የዩክሬን እና የአሜሪካ ልዑካን ባለፉት ሳምንታት ላሳዩት መቀራረብ ከፍተኛ አድናቆት አለን” ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ እአአ በየካቲት 2022 ዩክሬንን ሙሉ በሙሉ የወረረች ሲሆን በአሁኑ ወቅት 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።
ሩሲያ በአብዛኛው የምትቆጣጠረውን የምሥራቅ ዩክሬን የዶንባስ ክልልን ከወታደራዊ ኃይል ነፃ ቀጠና ለመቀየር የቀረበው ሀሳብ አሁንም “አልተፈታም” ሲሉ ትራምፕ ተናግረዋል።
ሞስኮ በአሁኑ ወቅት 75 በመቶ የሚሆነውን የዶኔትስክ ክልል እና 99 በመቶ የሚሆነውን የሉሃንስክ ክልል ትቆጣጠራለች። ክልሎቹ በአንድነት ዶንባስ በመባል ይታወቃሉ።
ታህሳስ 20/2018 ዓ.ም
