“በቴል አቪቭ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ ሳይንቲስቶች የታካሚን የሰውነት ስብ በመጠቀም፣ በ3D ፕሪንተር የታተመ አነስተኛ የሰው ልብ መስራት መቻላቸውን አስታውቀዋል።
ይህ በቤተ-ሙከራ ውስጥ የበቀለው ልብ፣ እንደ እውነተኛ የሰው ልጅ ልብ ሁሉ የደም ዝውውር ቱቦዎች፣ የልብ ክፍሎች እና ጡንቻዎች ያሉት ሲሆን፤ በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥም የመኮማተርና የመዘርጋት እንቅስቃሴ እንደሚያሳይ ተረጋግጧል።
ግኝቱ ይበልጥ ልዩ የሚያደርገው፣ ልቡ የታተመው ከታካሚው የራሱ የሰውነት ህዋሳት በመሆኑ፣ የሰውነት በሽታ መከላከል ስርአት አዲሱን አካል ‘ባዕድ ነው’ ብሎ የመግፋት እድሉን በእጅጉ የሚቀንስ መሆኑ ነው።
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት፤ ግኝቱ ወደፊት በሰው ሰራሽ መንገድ የአካል ክፍሎችን በማምረት፣ በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን የልብ ለጋሽ እጥረት ለመፍታት ትልቅ በር ይከፍታል።
ምንም እንኳን አሁን የታተመው ልብ መጠን አነስተኛ በመሆኑ ለንቅለ-ተከላ ባይበቃም፣ ግኝቱ በሰው ሰራሽ የአካል ክፍሎች ዝግጅት ረገድ ትልቅ ምዕራፍ መሆኑ ተገልጿል።
ሳይንቲስቶቹ በቀጣይ ልቡ ደም የመርጨት አቅሙ እንዲጎለብትና መጠኑም እንዲያድግ የሚያስችሉ ተጨማሪ ጥናቶችን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።”
ልኡል ወልዴ
ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም
