ያልተገቡ የኬላ ክፍያዎች ለኑሮ ውድነት መባባስ ምክንያት መሆናቸው ተነገረ

በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በተለያዩ መንገዶች ላይ የሚሰበሰቡ ያልተገቡ የኬላ ክፍያዎች በትራንስፖርት ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ጫና ከመፍጠራቸው ባለፈ ለሸማቹ ማህበረሰብ የኑሮ ውድነት ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸዉን የጣና ከባድ መኪና አሽከሪካሪዎች ማህበር ዋና ጸሃፊ አቶ ሰጡ ብርሃን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት አሽከርካሪዎች በየኬላው ለተለያዩ ምክንያቶች የሚከፍሉት ገንዘብ ከጭነት ታሪፋቸው ላይ እንዲጨምሩ እያደረጋቸው መሆኑ ተነግሯል።

ይህ ደግሞ በቀጥታ ወደ ሸማቹ ማህበረሰብ የሚሸጋገር በመሆኑ በምርቶች ዋጋ ላይ ጭማሪ እያመጣ ይገኛል ብለዋል አቶ ሰጡ።

በተለይም በኦሮሚያ ክልል እንደ ሞጆ፣ ኮካ እና አለም ጤና ባሉ አካባቢዎች የኬላ ክፍያዎች በአሽከርካሪዎች ላይ ትልቅ ጫና እየፈጠሩ መሆኑ ተጠቁሟል።

ከዚህ ቀደም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር፤ የኬላ ክፍያ የመንግስት ፍላጎት ሳይሆን የጥቂት ግለሰቦች ፍላጎት ነው ማለቱን ያስታወሱት የማህበሩ ፀሀፊ፤ መንግስት ይህንን ህገ-ወጥ አሰራር ለማስቆም ቁርጠኝነት ሊኖረው እንደሚገባ አሳስበዋል።

አሽከርካሪዎች በሀገሪቱ በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸው ሊከበር እንደሚገባና በየመንገዱ የሚፈጸሙ የገንዘብ ብዝበዛዎች በአስቸኳይ ሊቆሙ እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ሊዲያ ደሳለኝ

ታህሳስ 21/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *