ዛሬ ማለዳ በኳታር በተካሄደው የኦሬዶ ዶሃ ማራቶን በሁለቱም ፆታዎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ተከታትለው በመግባት ድል አድርገዋል።
በወንዶቹ አትሌት ታምራት ቶላ የቦታውን ሪከርድ ጭምር በመስበር አሸንፏል። የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤቱ ርቀቱን ለመጨረስ የፈጀበት ጊዜ 2:05.37 ሲሆን በዚህም በ2023 በሞሮኳዊው ማውሲን አውታልሃ 2:06.49 በሆነ ሰዓት ተይዞ የነበረውን የውድድሩን ሪከርድ ሊሰብረው ችሏል።
41ኛው ኪሎሜትር ድረስ ከፍተኛ ፉክክር በታየበት በዚህ ውድድር ታምራት ቶላ አፈትልኮ በመውጣት ቀሪውን አንድ ኪሎሜትር ብቻውን በመሮጥ ቀዳሚ ሆኖ ለመግባት ችሏል።
ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶችም እሱን ተከትለው በመግባት የድል ባለቤት ሆነዋል። እንደውም ከ1-10 ባለው ደረጃ ስምንት ኢትዮጵያውያን መካተት ችለዋል። ቀሪዎቹ ሁለት ቦታዎች በኤርትራና ኬንያ አትሌቶች የተያዙ ናቸው።
ደረጃቸውም የሚከተለውን ይመስላል፦
- ታምራት ቶላ 🇪🇹 2:05.37
- አሰፋ ቦኪ 🇪🇹 2:05.51
- ቦኪ ድሪባ 🇪🇹 2:06.22
- ድንቅዓለም አየለ 🇪🇹 2:06.38
- ባለው ይሁንልኝ 🇪🇹 2:07.02
- እቁባይ ክብሮም 🇪🇷 2:07.51
- ሙሉጌታ ደባሱ 🇪🇹 2:09.45
- ደሳለኝ ግርማ 🇪🇹 2:10.39
- ኒኮላስ ኪርዋ 🇰🇪 2:10.52
- ውበት ገ/ህይወት 🇪🇹 2:12.01
በሴቶቹ ምድብም በተመሳሳይ ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ተከታትለው በመግባት የድል ባለቤት ሆነዋል።
ትዕግስት ገዛኸኝ 2:21.10 በሆነ ጊዜ ቀዳሚ ሆና ስትገባ በ2023 በሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት መሰረት በለጠ 2:20.46 በሆነ ሰዓት የተያዘውን የቦታውን ሪከርድ ለመስበር 26 ሰከንዶች ብቻ ቀርተዋታል። ለአሸናፊነቱ ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷት የነበረችው ትዕግስት ግርማ (2:22.30) በሁለተኛነት አጠናቅቃለች።
ልክ እንደ ወንዶቹ ሁሉ በሴቶቹም ከ1-10 ባለው ደረጃ ውስጥ ከሁለት ኬንያውያት በስተቀር ሁሉንም ቦታዎች ኢትዮጵያውያት አትሌቶች ተቆጣጥረውታል።
- ትዕግስት ገዛኸኝ 🇪🇹 2:21.10
- ትዕግስት ግርማ 🇪🇹 2:22.30
- ጉታ አብዮት 🇪🇹 2:23.17
- ሙሉሀብት ፀጋ 2:23.18
- አማና ሙርሲ 🇰🇪 2:23.39
- ሮማን ግደይ 🇪🇹 2:25.26
- ሲላህ ሚቴይ 🇰🇪 2:25.35
- አለምፀሀይ መኩሪያ 🇪🇹 2:26.13
- ሀመልማል ታገል 🇪🇹 2:26.31
- ስንታየሁ ለውጠኝ 🇪🇹 2:28.52
ማስታወሻ፦ የውድድሩ አሸናፊዎች እንደየደረጃቸው የሚከፋፈሉት አንድ ሚሊዮን የኳታር ሪያል በሽልማት መልክ ይከፋፈላሉ። ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም ፆታዎች ቀዳሚ ሆነው የገቡት ሁለቱ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች Toyota Prado 2026 ቅንጡ መኪና በሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
ምስጋናው ታደሰ
ጥር 08/2018 ዓ.ም
