የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 52ኛ መደበኛ ስብሰባዉ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የጉምሩክ አዋጅን እንደገና ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡
በሥራ ላይ ያለው የጉምሩክ አዋጅ ለበርካታ ዓመታት ያገለገለ በመሆኑ፣ የአዋጁን ድንጋጌዎች ዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ከደረሰበት የዕድገት ደረጃ ጋር ለማጣጣም፣ በአገራችን እያደገ የመጣውን የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ለመደገፍ፣ እንዲሁም ሕጋዊ ንግድንና ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ይቻል ዘንድ የማሻሻያ አዋጁ ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን፤ምክር ቤቱም አዋጁ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

ለኢንቨስትመንት ስለሚሰጥ የታክስና ቀረጥ ማበረታቻ ረቂቅ ደንብ ምክር ቤቱ በቀጣይ የተወያየበት ጉዳይ ነው፡፡
ለሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላላቸውና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው፣ እንዲሁም ከፍተኛ ካፒታል ለሚጠይቁ የኢንቨስትመንት መስኮች በሥራ ላይ የሚውለውን ካፒታል ከግምት ውስጥ የሚያስገባና በአፈጻጸም ላይ የተመሠረተ የኢንቨስትመንት ማበረታቻ ሥርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ረቂቅ ደንቡ ተዘጋጅቶ ቀርቧል ነዉ የተባለዉ፡፡
ምክር ቤቱ ደንቡ በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተግባራዊ እንዲደረግ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የኢንተርፕረነርሽፕ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ነው፡፡
ፖሊሲው በኢንተርፕረነርሽፕ ዘርፍ የሚከናወኑ ተግባራት ቀጣይነት ኖሯቸው ለሀገራዊ የልማት ግቦች ስኬት ሚናቸውን እንዲወጡ፣ የፈጠራ ባህልን ለማጎልበትና እሴትን ለመጨመር የሚያስችል ምቹ የኢንተርፕረነርሽፕ ሥነ-ምህዳር ለመገንባት እንዲቻል ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
ምክር ቤቱም በፖሊሲው ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብዓቶችን በማከል፣ ፖሊሲው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ከጸደቀበት ከዛሬ ጥር 12 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

ጥር 12/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *