የቀድሞውን የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤን የገደለው ሰው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የ45 ዓመቱ ቴትሱያ ያማጋሚ በሐምሌ 2022 በምዕራባዊቷ ናራ ከተማ የምርጫ ቅስቀሳ ንግግር በማድረግ ላይ ሳሉ አቤን መግደሉን አምኗል።

እንደ ኤን ኤች ኬ ዘገባ ከሆነ፤የጃፓን ፍርድ ቤት የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤን መግደሉን ያመነውን ሰው ዛሬ በዕድሜ ልክ እስራት ቀጥቷል።

ከጃፓን ተፅዕኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት አቤ፣ በ2022 በምዕራባዊቷ ናራ ከተማ ለምርጫ ቅስቀሳ በማድረግ ላይ ሳሉ በተገደሉበት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣናቸውን ለቀው እንደ የፓርላማ አባል እያገለገሉ ነበር።

የ45 ዓመቱ ቴትሱያ ያማጋሚ በጥቅምት ወር በጀመረው የፍርድ ሂደት ግድያ መፈጸሙን አምኗል። የናራ ወረዳ ፍርድ ቤትም በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ መሠረት ያማጋሚን ጥፋተኛ ብሎ በዕድሜ ልክ እስራት ቀጥቶታል።

ጉዳዩ በጃፓን ገዥ ፓርቲ እና አወዛጋቢ በሆነው የደቡብ ኮሪያ ቤተክርስቲያን መካከል ለዘመናት የቆየውን የጠበቀ ግንኙነት ይፋ አድርጓል።

ያማጋሚ አቤን የገደለው የቀድሞው መሪ ከዩኒፊኬሽን ቤተክርስቲያን ጋር ግንኙነት ላለው ቡድን የላኩትን የቪዲዮ መልዕክት ካየ በኋላ መሆኑን ተናግሯል።

አክሎም ዓላማው የሚጠላውን ቤተክርስቲያን መጉዳት እና ከሺንዞ አቤ ጋር የነበረውን ግንኙነት ማጋለጥ እንደነበር ገልጿል።

ግድያው ባለሥልጣናት ለታዋቂ ሰዎችና ለከፍተኛ አመራሮች የሚደረገውን የፖሊስ ጥበቃ እንዲያጠናክሩም አድርጓል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለያማጋሚ ምሕረት እንዲደረግለት የሚጠይቅ አቤቱታ የፈረሙ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ ለዘመዶቹ እና እሱ ለሚገኝበት ማቆያ ማዕከል የእርዳታ ቁሳቁሶችን ልከዋል ሲል አሶሼትድ ፕረስ ነዉ የዘገበዉ።

እስከዳር ግርማ

ጥር 13/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *