የሚኒያፖሊስ ከተማ ነዋሪዎች አሁንም ተቃውሞዎች ማሰማታቸውን ቀጥለዋል

የአሜሪካ የፌደራል ኃይሎች በቀናት ልዩነት ቅዳሜ ዕለት ሁለተኛ ሰው መግደላቸውን ተከትሎ፤ ሚኒሶታ ውስጥ የምትገኘው ሚኒያፖሊስ ከተማ ነዋሪዎች እና አመራሮች ከፌደራል የጸጥታ አካላት ጋር መጋጨት ቀጥለዋል።

የሚኒሶታ ገዢ ቲም ዋልዝ፤ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሚኒሶታ ውስጥ ያሰማሯቸውን “3,000 ያልሰለጠኑ ኃይሎች” እንዲያስወጡ ጠይቀዋል።

ቅዳሜ ዕለት ከፌደራል ኃይል በተተኮሰ ጥይት የተገደለው አሌክስ ፕሪቲ የተባለው ግለሰብ የጽኑ ሕክምና ክፍል ነርስ እንደነበር ተገልጿል። የሚኒያፖሊስ ከተማ ነዋሪዎች የ37 ዓመቱን አሜሪካዊ ግድያ በመቃወም ሰልፍ ወጥተዋል።

ሰልፈኞቹ መጀመሪያ ላይ ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተው የነበረ ቢሆንም ኋላ የተደረጉት ተቃውሞዎች ግን ሰላማዊ ሆነው ቀጥለዋል። ነዋሪዎች ከሰልፍ እና ተቃውሞው በተጨማሪ መንገዶች ላይ ሟቹን ግለሰብ የሚዘክሩ መታሰቢያዎችን እያኖሩ ነው።

የሚኒሶታ ገዢ ቲም ዋልዝ በበኩላቸው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ያሰማሯቸውን “3,000 ያልሰለጠኑ ኃይሎች” ከግዛቱ እንዲያስወጡ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።

“እኛ በሰላም እናምናለን፤ [የፌደራል ኃይሎች] ሌላ ሰው ከመግደላቸው በፊት ዶናልድ ትራምፕ እነዚህን 3,000 ያልሰለጠኑ ኃይሎች ማስወጣት እንዳለባቸው እናምናለን” ብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በአንጻሩ የሚኒሶታ ባለሥልጣናት ግዛቱ ውስጥ የሚካሄደውን የፋይናንስ ማጭበርበር ምርመራ ጋር በተያያዘ “የወንጀል ሽፋን” ውስጥ ተሳትፈዋል ሲሉ ያለማስረጃ ከስሰዋል። የዋይት ሃውስ የፕሬስ ፀሐፊ ካሮሊን ሌቪትም የሚኒሶታ ገዢ “ዋልዝ ሁከትን ይፈልጋል” ወንጅለዋል።

ጥር 18 2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *