ተመራማሪዎች እስካሁን ከተገኙት ሁሉ እጅግ ግዙፍ የሆኑ የዳይኖሰር እግር አሻራዎችን አግኝተዋል ነዉ የተባለዉ።
አሻራዎቹ በጣም ግዙፍ ከመሆናቸው የተነሳ አንድ አዋቂ ሰው ያለምንም ችግር በውስጣቸው ሊተኛ ይችላል።
ይህ ጥንታዊ አሻራ በምዕራብ አውስትራሊያ በሚገኘው የዳምፒየር መሬት የተገኘ ሲሆን፤ በጊነስ የዓለም ክብረ ወሰን መዝገብ ላይ ‹‹የዓለም ትልቁ የዳይኖሰር እግር አሻራ›› የሚል መጠሪያ ተሰጥቶታል።
አሻራዎቹ በግምት ከ1መቶ30 ሚሊየን ዓመታት በፊት በነበረው የጥንቱ ክሪታሺየስ ዘመን በነበረ የአሸዋ ድንጋይ ውስጥ ተቀርጸው ይገኛሉ።
አሻራዎቹ የተለያዩ ቅርጾች ያሏቸው ሲሆኑ፤በሰሜን ምዕራብ አውስትራሊያ ይዘዋወሩ የነበሩትን የተለያዩ የዳይኖሰር ዓይነቶች የሚያሳዩ ናቸዉ፡፡
በዚህ ቦታ ላይ 1.7 ሜትር ርዝመት ያለው የ‹‹ሶሮፖድ›› ዳይኖሰር እግር አሻራ ተገኝቷል። ይህም እስካሁን በዓለም ላይ ከተገኙት የዳይኖሰር እግር አሻራዎች ሁሉ ትልቁ ነው።
የኩዊንስላንድ ዩኒቨርሲቲ እና የጄምስ ኩክ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች እነዚህን ግዙፍ አሻራዎች አንድ ወቅት በምድር ላይ ይዘዋወሩ ከነበሩት ረጅም አንገት ካላቸውና ዕፅዋት ተመጋቢ ከሆኑት ሶሮፖድ ከተባሉ ግዙፍ ዳይኖሰሮች ጋር አያይዘዋቸዋል።
አሻራዎቹን ጥለው ያለፉት ዳይኖሰሮች በዳሌያቸው በኩል ብቻ ቁመታቸው ከ5.3 እስከ 5.5 ሜትር ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል። ይህም ለዳይኖሰሮች እንኳ ቢሆን እጅግ በጣም ግዙፍ የሚባል መሆኑን ተመራማሪዎች መግለጻቸዉን ጠቅሶ ሲኤን ኤን ነዉ የዘገበዉ፡፡
እስከዳር ግርማ
ጥር 21/2018 ዓ.ም
