በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን፣ የሙስና ሰንሰለቶችን እና በህዝብ ሀብት ላይ የሚፈጸሙ እክሎችን ለመፍታት ጥብቅ የሪፎርም ስራ እንደሚሰራ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
ከንቲባዋ ይህንን ያሉት አስተዳደራቸው የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት አፈፃፀም ግምገማ ላይ ባደረጉት የማጠቃላያ ንግግር ነው፡፡
በገቢዎች ቅርንጫፍ ቢሮዎች አካባቢ የሚስተዋሉ የአክብሮት ጉድለት፣ ሆን ብሎ ባለጉዳይን ማጉላላት እና ተገቢ ያልሆነ ምላሽ የመስጠት ችግሮች በአፋጣኝ እንደሚፈተሹም አሳስበዋል።
በተለይም ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በሚገኙ የቅሬታ መስሚያ መንገዶች የቀረቡ አቤቱታዎችን መሰረት በማድረግ ግዴታቸውን የማይወጡ ሰራተኞች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ሲሉ ተናግረዋል ።
በነፃ ሊሰጡ የሚገባቸውን የመንግስት አገልግሎቶች ለግል ጥቅም መለወጫ ያደረጉ፣ ከደላሎች ጋር በመቀናጀት አሰራርን የሚያጓትቱ የቡድን መሪዎችና ዳይሬክተሮች ተለይተው “አግሬሲቭ” የሆነ እርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተጠቁሟል።
የከተማ አስተዳደሩ በፖለቲካ ስርዓት ለውጥ የማይናወጥ፣ ጠንካራ እና በሲስተም የሚመራ ሲቪል ሰርቪስ ለመገንባት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም ከንቲባዋ አሳውቀዋል።
በመጨረሻም፣ አመራሩ በስነ-ምግባርና በውጤታማነት ምሳሌ መሆን እንዳለበትና ህዝቡም ብልሹ አሰራሮችን በመጠቆም በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።
ሀና ሰይፉ
ጥር 21/2018 ዓ.ም
