የአሜሪካዉ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ይህንን የተናገሩት፤ የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ለሦስተኛ ቀን የቻይና ጉብኝታቸው ሻንጋይ በገቡበት ወቅት ነዉ፡፡
ዩኬ ከቻይና ጋር የንግድ ግንኙነት መፍጠሯ ‹‹በጣም አደገኛ››ነው በማለት ሁኔታውን አብራርተዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነትን ለማሳደግ ስምምነቶች የተደረጉ ሲሆን፤ ትራምፕ ለሰጡት አስተያየት ምላሽ የሰጠው የብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በበኩሉ ዋሽንግተን ስለ ጉዞው እና ስለ ዓላማው አስቀድሞ መረጃ እንደነበረው በመግለፅ ፤ፕሬዝዳንት ትራምፕ ራሳቸው በሚያዝያ ወር ቻይናን እንደሚጎበኙ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጠቁሟል።
ትራምፕ ስለ እንግሊዝ የንግድ ግንኙነት በጋዜጠኞች ከተጠየቁ በኋላ በሰጡት ምላሽ፤ ስለ ዩኬ እና ቻይና ግንኙነት ተጨማሪ አስተያየት ከመስጠት ቢቆጠቡም ንግግራቸውን ወደ ካናዳ በማዞር ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡
ለካናዳ ደግሞ የበለጠ አደገኛ ይመስለኛል ያሉት ትራምፕ፤ ካናዳ በጥሩ ሁኔታ ላይ አይደለችም፤ በጣም ደካማ አፈጻጸም እያሳየች ነው እናም ቻይናን እንደ መፍትሄ ማየት የማይቻል ነው በማለት ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ትራምፕ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ በቅርቡ ቤጂንግን በጎበኙበት ወቅት ከተደረሱት የኢኮኖሚ ስምምነቶች ጋር ካናዳ የምትቀጥል ከሆነ ታሪፍ እንደሚጥሉባትም ዝተዋል ያለዉ ቢቢሲ ነዉ።
ሀና ሰይፉ
ጥር 22/2018 ዓ.ም
