ቻይናዊው ብሎገር በሺዎች ከሚቆጠሩ የሲም (SIM) ካርዶች እና ከኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች 191 ግራም ወርቅ አወጣሁ አለ፡፡

አንድ ቻይናዊ ብሎገር በቅርቡ ከሲም ካርዶች እና ከሌሎች የኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻዎች በግምት ከ120,000 ዩዋን (17,000 ዶላር) በላይ የሚያወጣ ወርቅ ማውጣቱን ገልጿል።

በጓንግዶንግ ግዛት የሚገኘው ይህ ብሎገር፣ በቆሻሻነት ከተጣሉ የሲም ካርድ ቺፖች እና የኤሌክትሮኒክስ አካላት ላይ እንደ “ጠንካራ አሲድ” እና “ኤሌክትሮላይቲክ ሪዳክሽን” ያሉ ውስብስብ ሂደቶችን በመጠቀም 191.73 ግራም ወርቅ ማውጣቱን ተናግሯል።

ይህን የ”ሲም አልኬሚ”ሂደት የሚያሳይ ቪዲዮ በማጋራቱም ተመልካቾች በጉዳዩ ላይ ትልቅ ፍላጎት እንዲያሳድሩ አድርጓል።

በቪዲዮው ላይ አስተያየት የሰጠ አንድ ሰው “አሥር ዓመት ከመሥራት አንድ ዓመት ቆሻሻ መሰብሰብ ይሻላል” በማለት ብሎገሩ ይህን “የቺፕ ወርቅ ማውጣት” ጥበብ እንዲያስተምረው ጠይቋል።

ሌላ ተመልካች ደግሞ “ከሲም ቺፖች ወርቅ መሥራት ይቻላል? ከዚህ በፊት ሰምቼ አላውቅም” ሲል ጽፏል።

የብሎገሩ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ከፍተኛ መነቃቃትን ቢፈጥርም፣ ባለሙያዎች ግን በአንድ የሲም ካርድ ቺፕ ውስጥ ያለው የወርቅ መጠን እጅግ በጣም አነስተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

ቪዲዮው በእያንዳንዱ ካርድ ውስጥ 0.02 ግራም ወርቅ አለ ቢልም፣ ትክክለኛው የወርቅ መጠን ግን 0.47 ሚሊግራም ብቻ ነው። ይህ ማለት ደግሞ 191 ግራም ወርቅ ለማግኘት ወደ 400,000 የሚጠጉ የሲም ካርዶችን ማሰባሰብ ያስፈልጋል ማለት ነው።

በቪዲዮው ዙሪያ የተነሳውን ውዝግብ ተከትሎ፣ የጓንግዶንግ ብሎገር ምላሽ ሰጥቷል። ወርቁን ለማውጣት የተጠቀመባቸው ቁሶች “ተራ የሲም ካርዶች” ብቻ ሳይሆኑ፣ ከመገናኛ ኤሌክትሮኒክስ ዘርፍ የተሰበሰቡ በወርቅ የተለበጡ የቆሻሻ ቺፖች መሆናቸውን አብራርቷል።

“ግልጽ ማድረግ የምፈልገው ይህ ታሪክ አንድ ግለሰብ ከተጣሉ ተራ የሲም ካርዶች ወርቅ ስለማውጣቱ የሚያወራ አይደለም” ብሏል ብሎገሩ። “ይህ ውድ ማዕድናትን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚከናወን ሕጋዊ ሂደት ነው። የቪዲዮው ዓላማም ሂደቱን እና መልሶ የመጠቀምን ፋይዳ ለማሳየት እንጂ መነጋገሪያ ለመፍጠር አልነበረም” ሲል ገልጿል።

ባለሙያዎች በበኩላቸው የብሎገሩን ፈለግ ለመከተል ለሚፈልጉ ሰዎች ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። በቪዲዮው ላይ የሚታየው የወርቅ ማውጣት ሂደት ከፍተኛ አደጋ የሚያስከትሉ ኬሚካሎችን መጠቀምን የሚጠይቅ በመሆኑ፣ ለደህንነት አስጊ ከመሆኑም በላይ አካባቢን የመበከል ከፍተኛ ዕድል እንዳለው አሳስበዋል።

ሐመረ ፍሬው

ጥር 22/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *