አንገትን ለማዝናናት ተብሎ የሚደረግ ቀላል እንቅስቃሴ አንዲት ወጣት የማየት እና የመናገር ችሎታዋን ለጊዜው እንድታጣ አድርጓታል።
ኬሊን ፌልታገር ከገበያ ወደ ቤቷ እየነዳች ሳለ የራስ ምታት ስለተሰማት ውጥረቱን ለመቀነስ አንገቷን ወደ ቀኝ በደመነብስ አሳሳበችው።
ከረጅም የሥራ ቀን በኋላ አንገትን ማሸት፣ ማንቋቋት ለእሷ የተለመደ ልማድ ነበር፤ ሆኖም በዚህኛው ጊዜ ሁኔታው የተለየ ሆነ።
አንገቷ ሲጮህ እንደሰማች ወዲያውኑ የሚወጋ ከፍተኛ ሕመም ተሰማት።
አንገቷ ላይ የተሰማት ሕመም የተለመደ አልነበረም፤ ለሚቀጥሉት ጥቂት ቀናትም አለመሻሻሉ ቢያሰጋትም ሐኪም ዘንድ ከመሄድ ይልቅ ያለ ማዘዣ የሚሸጡ የሕመም ማስታገሻዎችን ብቻ ስትወስድ ቆየች።
ከአምስት ቀናት በኋላ ግን ነገሩ የባሰ መልክ ያዘ።
ኬሊን ለቀጠሮ ለመውጣት ሜካፕዋን እየተቀባች ሳለ፣ በድንገት ብሩህ ብርሃን በዓይኗ ፊት ብልጭ አለና የማየት ችሎታዋን አጣች።
ዓይኗን ደጋግማ ብታርገበግብም ሊሻላት አልቻለም።
ሆኖም ከ15 ደቂቃ በኋላ እይታዋ ስለተመለሰ እንደ አንድ አጋጣሚ ቆጥራ ችላ አለችው።
ያጋጠማትን ስታስታውስ በቀኝ ዓይኔ በኩል የሚታወር ብርሃን መጣና እይታዬ ጠፋ፤ ብሩህ ብርሃን እንጂ ሌላ ምንም ነገር ማየት አልቻልኩም ነበር ትላለች።
እይታዋን ካጣች ከጥቂት ጊዜ በኋላ መላው ቀኝ የሰውነቷ ክፍል የመደንዘዝ ስሜት ተሰማት።
ነገር ግን የሆነ ትልቅ ችግር እንዳለ የተረዳችው ንግግሯ መዛባት ሲጀምር ነው።
ቃላትን በሥርዓት መጥራት አቅቷት የሚንተባተብና የማይገባ ንግግር ስታወጣ፣ ባለቤቷ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ወሰዳት።
ሆስፒታል እንደደረሰች የተደረገላት የሲቲ ስካን ምርመራ ውጤት የስትሮክ አደጋ እንደደረሰባት አረጋገጠ።
ከጥቂት ቀናት በፊት በመኪና ውስጥ አንገቷን ስታሳስብ ስለተሰማት ሕመም ለሕክምና ባለሙያዎቹ ካስረዳች በኋላ፣ ያ ያደረገችው ቀላል የሚመስል የአንገት ማሳሳብ በደም ሥሯ ላይ መቀደድ እንዳስከተለና ይህም በኋላ ወደ አዕምሮዋ የሚሄድ የደም መርጋት ፈጥሮ ለስትሮክ እንደዳረጋት ተነገራት።
እንደ ዕድል ሆኖ የረጋው ደም በፍጥነት በመሟሟቱ ዶክተሮቹ ቀዶ ህክምና ማድረግ አላስፈለጋቸውም።
ኬሊን ፌልታገር በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ አገግማለች።
ሆኖም ይህ ተሞክሮ ስለ ሰውነቷ ያላትን አመለካከትና ነገሮች ምን ያህል በፍጥነት ሊበላሹ እንደሚችሉ ያላትን ግንዛቤ እንደቀየረው ትናገራለች።
አንገት በጣም ስስ የሰውነት ክፍል በመሆኑ፣ እንደ አንገትን በፍጥነት ማዞር ያሉ ቀላል እንቅስቃሴዎች እንኳን ለከፋ የስትሮክ አደጋ ሊያጋልጡ ይችላሉ ያለው የኦዲቲ ሴንትራል ዘገባ ነው።
ሀና ሰይፉ
ጥር 28/2018 ዓ.ም
