በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በሚገኘው አደን አብዱሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፣ አንድ 55 ሰዎችን የጫነ የመንገደኞች አውሮፕላን አስቸኳይ ማረፊያ ለማድረግ ሲሞክር ከማኮብኮቢያው ወጥቶ የባሕር ዳርቻ ላይ ቢያርፍም፣ በሰው ሕይወት ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩ ተገልጿል።
ፎከር 50 የተሰኘውና የስታርስኪ አቪዬሽን (Starsky Aviation) ንብረት የሆነው ይህ አውሮፕላን፣ ትላንት ማክሰኞ ከሞቃዲሾ ተነስቶ ወደ ሰሜናዊቷ ጋልካዮ ከተማ ጉዞ መጀመሩ ታውቋል።
ሆኖም በረራ ከጀመረ ከ15 ደቂቃዎች በኋላ የቴክኒክ ችግር እንዳጋጠመው ፓይለቱ ለበረራ መቆጣጠሪያ ማዕከል በማሳወቁ፣ ወደ ተነሳበት አውሮፕላን ማረፊያ እንዲመለስ ተደርጓል።
አውሮፕላኑ አደን አብዱሌ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ለማረፍ ሲሞክር ከማኮብኮቢያው በመውጣት፣ በአቅራቢያው በሚገኘው የህንድ ውቅያኖስ ጥልቀት በሌለው የባሕር ዳርቻ ላይ አርፏል።
በአደጋው የአውሮፕላኑ ክንፍና የፊት ለፊት ክፍል (አፍንጫ) ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም፣ በውስጡ የነበሩት 55 መንገደኞችና የበረራ ሰራተኞች በሙሉ በሰላም መውጣታቸው ተረጋግጧል።
የስታርስኪ አቪዬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ አህመድ ኑር ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ፓይለቱ ለበረራ መቆጣጠሪያ ማዕከሉ በወቅቱ መረጃ በመስጠትና የነበረውን አስቸጋሪ ሁኔታ በሙያዊ ብቃት በመወጣቱ የሰዎችን ሕይወት ማዳን ተችሏል ብለዋል።
የሶማሊያ ትራንስፖርት ሚኒስትር መሐመድ ፋራህ ኑህ በበኩላቸው፣ በአደጋው በአውሮፕላኑ ላይ እንጂ በሰው ላይ የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን አረጋግጠው፣ የአደጋውን መንስኤ በዝርዝር ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ገልጸዋል።
በአደጋው ወቅት በአቅራቢያው የነበሩ የአፍሪካ ህብረት እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ አባላት ከነፍስ አድን ሰራተኞች ጋር በመሆን ተሳፋሪዎችን በማውጣት ረገድ ፈጣን ድጋፍ ማድረጋቸው ተገልጿል ያለዉ አፍሪካ ኒዉስ ነዉ።
ልዑል ወልዴ
የካቲት 04/2018 ዓ.ም
