ኔታንያሁ እና ትራምፕ የኢራን የኒውክሌር ድርድር ወሳኝ ደረጃ ላይ በደረሰበት በዚህ ወቅት ሊገናኙ ነው ተባለ

በመካከለኛው ምስራቅ ያለው ውጥረት እየጨመረ በመጣበት እና የኢራንን የኒውክሌር መርሃ ግብርን ለመገደብ የሚደረገው ድርድር በጠነከረበት ወቅት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የእስራኤሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁን ዛሬ በኋይት ሀውስ ያስተናግዳሉ።

ኔታንያሁ ኢራን ዩራኒየም የማበልጸግ ስራዋን እንድታቆም እንዲሁም እንደ ሃማስ እና ሄዝቦላህ ላሉ ተላላኪ ቡድኖች የምታደርገውን ድጋፍ እንድትገታ የሚያስገድድ ስምምነት እንዲደረግ በትራምፕ ላይ ጫና ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኔታንያሁ ወደ አሜሪካ ከመነሳታቸው በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ እነዚህን ድርድሮች በተመለከተ ያለንን አመለካከት ለፕሬዝዳንቱ አቀርባለሁ ብለዋል።

ኢራን በበኩሏ ምዕራባውያን ሀገራት በኢኮኖሚዋ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ ካላላሉ በስተቀር የዩራኒየም ማበልጸግ ስራዋን እንደማትገድብ አስታውቃለች።

ይህ ጉብኝት ኔታንያሁ ትራምፕ ወደ ስልጣን ከተመለሱ በኋላ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉት ስድስተኛው ጉዞ ሲሆን፤ ይህም ከማንኛውም የአለም መሪ የበለጠ ወደ አሜሪካ ለጉብኝት የተጓዙ መሪ ያደርጋቸዋል።

ጉብኝቱ የመጣው አሜሪካ በመካከለኛው ምስራቅ የጦር ሃይል እያጠናከረች ባለችበት ወቅት ሲሆን፤ ትራምፕ ኢራን በኒውክሌር ጉዳይ ላይ ስምምነት ላይ ካልደረሰች እርምጃ እንደሚወሰድባት አስጠንቅቀዋል።

ትራምፕ በሰጡት ቃለ ምልልስ፤ አንድ ትልቅ የጦር መርከቦች ስብስብ ወደዚያ እያመራ ነው፣ ሌላም ሊሄድ ይችላል ያሉ ሲሆን፤ ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎችን መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል።

ሀና ሰይፉ

የካቲት 04/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *