ኢራን የኒውክሌር ኃይልን በሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም ቁርጠኛ መሆኗን ገለጸች

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል ባጋሃይ፤ አገራቸው የኒውክሌር ጦር መሣሪያዎች እንዳይስፋፉ የሚከለክለው ስምምነት ቁርጠኛ አባል መሆኗንና ግዴታዎቿን እንዲሁም መብቶቿን መቀበሏን ገልጸዋል።

በጄኔቫ ከሚካሄደው ድርድር በፊት ለኢርና የዜና ወኪል እንደተናገሩት፤ በስምምነቱ አንቀጽ 4 መሠረት መብታችን የኒውክሌር ኢነርጂን ለሰላማዊ ዓላማ መጠቀም ሲሆን፤ ዩራኒየም የማበልጸግ ሂደትም የዚሁ አካል ነው ብለዋል።

ስለ ድርድሩ በሰጡት አስተያየትም፤ ቴህራን ንግግሩን በተቻለ ፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደምትፈልግና ለዚህም ሲባል አስፈላጊው የሰው ኃይል በሙሉ በስዊዘርላንድ ከተማ እንዲገኝ ማድረጓን ተናግረዋል።

በዚህኛው ዙር ድርድር የተሟላ ቡድን ይዘን እንቀርባለን፤ ይህም የፖለቲካ፣ የሕግ፣ የኢኮኖሚ እና የቴክኒክ ቡድንን ያካትታል ያሉት ቃል አቀባዩ፤ እየተደራደርን ያለነው ሙሉ በሙሉ ጥርጣሬ እና አለመተማመን በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ ነው ሲሉ ለኢርና ገልጸዋል።

ባጋሃይ አክለውም፤ ያለፉ ተሞክሮዎች አሉን፤ እነዚህን ተሞክሮዎች ደግሞ በማንኛውም ሁኔታ ለአፍታም ቢሆን ከዓይናችን ልናርቃቸው አይገባም ብለዋል ሲል አልጀዚራ ዘግቧል።

ሊዲያ ደሳለኝ

የካቲት 10/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *