በትግራይ ክልል በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቀመጡ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች በክልሉ ለማካሄድ ለታሰበዉ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አስቻይ ሁኔታ እንዳይፈጠር አድርጓል ተባለ

በትናንትናው ዕለት የአራት አመታት የስራ ክንዉን አፈፃፀሙን ለእንደራሴዎቹ ምክር ቤት አባላት ገለፃ ያደረገዉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮምሽን በትግራይ ክልል እያደረገ ስላለዉ ስራ ማብራሪያ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮምሽነር ኘሮፌሰር መስፍን አርአያ በሰጡት ማብራሪያ፥ክልሉ ላይ የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ኮሚሽነሩ ሲቀጥሉም “በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊዎች ልየታ ለማካሄድ አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተለያዩ  ቅድመ ሁኔታዎች በመቀመጣቸዉ ምቹ ሁኔታ አልተፈጠረም ” ሲሉ ተናግረዋል።

ከተደረገዉ የፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ቀድሞ ከነበሩት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ጀምሮ በአሁን እስካሉት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ድረስ ኮምሽኑ በርካታ ስብሰባዎችን አድርጓል ሲሉ ኘሮፌሰር መስፍን ገልፀዋል።

በዉይይቶቹ የመተማመን ፈጠራ ሂደት እንዲኖር ለማድረግ ኮምሽኑ ጥረቶች አድርጓል ተብሏል።

“ከአሁኑ ጊዜያዊ አስተዳደር ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ በተሰጠ ምክረ ሀሳብ መሠረት በክልሉ ባሉ  በአምስቱ የዞን ዋና ከተሞች መቀሌ፣አክሱም፣ አዲግራት፣ማይጨዉ እና ሽሬ ማድረግ ትችላላችሁ በሚል መልካም ሀሳብ ተሰጥቶ ነበር ” ሲሉ ያስረዱት ፕሮፌሰር መስፍን፥
ሆኖም ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ሁኔታ በተፈጠሩ አንዳንድ ሁኔታዎች ለመጀመር ፍቃድ አላገኘንም ሲሉም አክለዋል።

የሀገራዊ ምክክር ኮምሽን ምክትል ኮምሽነር ሂሩት ገብረ ስላሴ በበኩላቸዉ ፥”በእስካሁኑ ስራ  በሌሎች ክልሎች በአማካኝ ሶስት ዙር መድረኮች የሚካሄድ ሂደት ነበር በትግራይ ክልል ግን በሀያ መድረኮች ሀሳብ እየተለዋጥን ቆይተናል “ብለዋል

ኮምሽኑ በክልሉ ካለሁ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የአጀንዳ ማሰባሰቡን ለማካሄድ ሌሎች  አማራጮችን እንደሚከተል እና ጥረቱ እንደሚቀጥል ገልጿል።

ቁምነገር አየለ

የካቲት 12/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *