ሀገራዊ የታሪክ ከፍታ ያላቸዉ የታሪክ ምዕራፎች ከግጭት ምንጭነት እንዲርቁ መጠበቅ ያስፈልጋል ተባለ

ለኢትዮጵያውያን የካቲት ወር የታሪካቸዉ ደማቅ ክፍል ነዉ ይባል እንጂ አሰቃቂ የተባለዉ የዜጎች እልቂት የተስተናገደበት ወር ነዉ።

የዛሬ 89 አመት የካቲት 12/1929 አዲስ አበባ በአሰቃቂ እልቂት የተዋጠችበት በሶስት ተከታታይ ቀናት ከሰላሳ ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን በሮዶልፍ ግራዚያኒ የጭካኔ በትር የተጨፈጨፉበት እለትም ነዉ።

የጥንታዊት ኢትዩጵያዊ ጀግኖች አርበኞች ማህበር 89ኛዉን የሰማእታት መታሰቢያ በአል ስድስት ኪሎ በሚገኘዉ ሀዉልት በመገኘት የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ አክብሯል።

ኢትዩ ኤፌም ያነጋገርናቸው በሀረማያ ዩንቨርስቲ የታሪክ መምህር የሆኑት ዶ/ር ረታ ድጉማ በኢትዮጵያ ታሪክ ተሰዉተዋል የምንላቸዉን ሰምአታት የሞቱለትን አላማ አሁን በሀገሪቱ አለመገኘቱን ገልፀዉ ህዝብ ማክበር÷ህዝብን ማድመጥ እና በዛም መንገድ መስራት እና ያንን መፍጠር ይገባል ሲሉም ሀሳባቸዉን ሰጥተዋል

አክለዉም ታሪክ ጥሩ ተሞክሮዎች አሉት የሚሉት ዶ/ር ረታ በኢትዮጵያ ዛሬም አወዛጋቢ ስለሚሆኑ የጋራ ጀግኖች እና ታሪኮች የግጭት ምንጭነትን ለመቀነስ ምሁራዊ እይታዎችን ሚዛናዊ አድርጎ ማቅረብ ተገቢ ስለመሆኑ ይገልፃሉ።

ሌላኛዉ ያነጋገርናቸዉ የየካቲት 12 ቱን ታሪክ ተንተርሶ የተፃፈዉን “the plot to kill Graziani” መፅሀፍ ዉርስ ትርጉም ያዘጋጁት የፖለቲካ እና አለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ የእዩብዘር ዘዉዴ ናቸዉ።

ባለሙያው የየካቲት 12ቱ እልቂት ጉልህ እና አሰቃቂ ሆኖ በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ያለ ትልቅ ጠባሳ መሆኑን እንዲሁም የትዉልድ ክፍተት የፈጠረ እንደነበር ይገልፃል።

በወቅቱ ከገጠመዉ የሀገር ግንባታ መናድ በኋላ የተጀመረችዉ አዲስ ኢትዮጵያ ነበረች የሚሉት አለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ ትናንትን በተሻለ መረዳት መቻል አሁን እንደ ሀገር ካለንበት ጭካኔ ሊያወጣን ይችላል ይላሉ።

ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ችግሮችን በንግግር ለመፍታት ልበቀናነት ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል።

“ብዙ ዋጋ የተከፈለለት ሀገር መሆኗ÷ ሀገርን ብለዉ ሺዎች የወደቁለት መሬት በመሆኗ ሺዎች እንዲኖሩበት ለማድረግ ደግሞ ሁላችንም ባለእዳ የመሆን ስሜቱ ሊኖረን ይገባል” ሲሉ የአለምአቀፍ ግንኙነት መምህሩ የእዩብዘር ዘዉዴ ተናግረዋል ።

ይህ እለት ዜጎች ከነፃነት ስለተፋታች ሀገራቸዉ እንዲሁም በሶስት ቀኑ በአዲስ አበባዉ ጭፍጨፋ መራር ሀዘን የወደቀበት እለት የሆነ የታሪክ ማስታወሻ ሆኗል።

ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች ኢትዮጵያ በተለያዩ መልክ ለሚነገርላት የነፃነት እንዲሁም የመስዋዕትነት ታሪክ ጀርባ ባሉ አላማዎች ማለትም የፍትሕ ÷ የሰብአዊነት መሰል መሰረት ላይ ሀገርን ማስቀጠል ይገባል ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።

89ኛዉ የሰማእታት መታሰቢያ በአል በዛሬዉ እለት ተዘክሯል።

ቁምነገር አየለ

የካቲት 12/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *