የፈረንሳዩ የራዲዮ ጣቢያ ፍራንስ ኢንፎ እንደዘገበው፤ የፓሪስ ሴንት ዠርመ ምክትል አምበል አሽራፍ ሀኪሚ በመድፈር ወንጀል ተከሶ ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነዉ፡፡
የናንቴሬ አቃቤ ሕግ ቢሮ፤ ለፓሪስ ሴንት ዠርመ እና ለሞሮኮ ብሔራዊ ቡድን በሚጫወተው ሀኪሚ ላይ የመድፈር ወንጀል ክስ ከቀረበ በኋላ በ2023 ምርመራ ከፍቶ ነበር።
በወቅቱም በፈረንሳይ የሕግ ሥርዓት መሠረት የመጀመሪያ ደረጃ ክስ ተከፍቶበት ነበር፡፡
ይህም ዳኞች ወንጀል ለመፈጸሙ ጠንካራ ጥርጣሬ አላቸው ማለት ቢሆንም፤ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ከመላካቸው በፊት ለተጨማሪ ምርመራ ጊዜ የሚሰጡበት ነዉ፡፡
በወቅቱ የሀኪሚ ጠበቃ ፋኒ ኮሊን ለአሶሺየትድ ፕሬስ በላኩት የጽሑፍ መልዕክት፤ ተጫዋቹ የቀረበበትን ክስ አጥብቆ አስተባብሏል ብለዋል።
ክሱን መጀመሪያ ይፋ እንዳደረገው ‹‹ለ ፓሪዚዬ››ጋዜጣ ዘገባ፣ክሱን ያቀረበችው የ24 ዓመት ወጣት በፓሪስ ዳርቻ በሚገኘው ቤቱ ውስጥ እንደደፈራት ገልጻለች።
አሁን ላይ አሶሼትድ ፕረስ ምላሻቸዉን ፈልጎ አስተያየት የጠየቃቸዉ የሀኪሚ ጠበቃ ለቀረበላቸው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጡም።
እስከዳር ግርማ
የካቲት 17/2018 ዓ.ም
