የዚህ የማሻሻያ አዋጅ ምርጫዉ ከመካሄዱ በፊት ከፀደቀ በምርጫው ላይ የራሱን ጥላ የሚያጠላ እንዲሆን ያደርገዋል ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን ኮምሽነር ብርሃኑ አዴሎ ተናገሩ።
በዛሬዉ ዕለት በኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በተሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ የማሻሻያ ረቂቁ በሂደት ላይ መሆኑን የገለፁት ኮምሽነሩ፤ የሲቪክ ምህዳሩ ጠበበ ከተባለ “ምርጫ ከመካሄዱ አስቀድሞ ማፅደቅ የሚያስተላልፈው መልእክት ሌላ ነዉ “ሲሉ ተናግረዋል።
የአዋጅ ማሻሻያ አሳሪ ህጎች እንደነበሩት ተደጋግሞ ሲገለፅ ቆይቷል፤ ዛሬ በተሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ ማብራሪያ የሰጡት ኮምሽነር ብርሃኑ አዴሎ ኮምሽኑ ሲያደርገዉ በቆየዉ የዉትወታ ስራ የአዋጁን የተወሰኑ ድንጋጌዎች ማለዘብ ተችሏል ብለዋል።
“መንግስት ማሻሻያ ሊያደርግ ከሆነ በሰፊዉ ዉይይት ተደርጎበታል ላዉጣዉ ቢል መንግስትን መከልከል አይቻልም ነገርግን አሁን ማዉጣቱ በምርጫ ላይ ጥላ ሊያጠላ ይችላል” ሲሉም አክለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮምሽን አዋጁ ከምርጫዉ በፊት እንዳይወጣ የዉትወታ ስራዉን እንደሚቀጥል ኮምሽነሩ ገልፀዋል።
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ የ “አፋኝ ህጎችን ስጋት ይፈጥራል” እንዲሁም የሲቪክ ምህዳሩን እንዳያጠበዉ የሚል ጥያቄ የተነሳበት መሆኑ የሚታወስ ነዉ።
ቁምነገር አየለ
የካቲት 17/2018 ዓ.ም
