- የጠቅላላ ምርጫ ምዝገባ በሀገር አቀፍ ደረጃ ቦርዱ በሚወስናቸው ቀናት የሚጀመርና የሚጠናቀቅ ይሆናል፡፡
- ቦርዱ የሚመለከታቸውን ክልሎች ሕገ መንግስት ወይም ሌሎች አግባብነት ያላቸውን ህጎች መነሻ በማድረግ የአካባቢ ምርጫዎችን የምዝገባ ጊዜ ሰሌዳ ያወጣል፡፡
- ቦርዱ በዚህ አንቀፅ ንኡስ አንቀፅ (1) እና (2) መሠረት የምዝገባ ቀናቱን ከመወሰኑ በፊት በምርጫው ከሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር እንደ አስፈላጊነቱም ከሲቪል ማህበራት፤ መገናኛ ብዙሃን እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ይመካከራል፡፡
- ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ የሚጀምርበትን ዕለት በምርጫ የጊዜ ሰሌዳው በማካተት ምዝገባው ከመጀመሩ 15 ቀን በፊት ጀምሮ ባሉት ቀናት በተከታታይ በመገናኛ ብዙሃንና በሌሎች የማስታወቂያ መንገዶች አማካኝነት የምዝገባውን ሰሌዳ ለህዝቡ ይገልፃል፡፡
- የመራጮች ምዝገባ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ቅዳሜ እና እሁድን ጨምሮ በፌደራል መንግስት ህጎች የተደነገጉ የሕዝብ በዓላትን ሳይጨምር በመደበኛ የመንግሥት የሥራ መግቢያና መውጫ ሰዓት መሰረት ይከናወናል፡፡
- የምርጫ አስፈጻሚዎቹ የየክልሉን መደበኛ የሥራ ሰዓት በመከተል ለአንድ ሰዓት ብቻ ለምሳ ይወጣሉ፡፡
- ቦርዱ በአንዳንድ ክልሎች ያለውን የመንግሥት የስራ ሰአት አፈፃፀም ህጎች ግምት ውስጥ ማስገባት የሚያስፈልግ ሆኖ ሲያገኘው የተለየ የስራ ሰዓት ሊወስን ይችላል።
የካቲት 24/2018 ዓ.ም
