በመካከለኛው ምስራቅ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ግጭት አዲስ መልክ እየያዘ መጥቷል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ኢራን ከሰሜን ኮሪያ በበለጠ ለዓለም አደገኛ መሆኗን ገልጸዋል፡፡
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በበኩላቸዉ እስራኤልን በአንድ ሚሳኤል ለማጥፋት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ኔታንያሁ ‹‹ኢራን 50 ሰሜን ኮሪያዎችን ትሆናለች›› ሲሉ ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ተደምጠዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የኢራንን አደገኝነት ሲያስረዱ ሰሜን ኮሪያን እንደ ማነፃፀሪያ ተጠቅመዋል።
ኔታንያሁ በንግግራቸው ሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳኤል እና የኒውክሌር ጦር ቢኖራትም፤ እንደ ኢራን “ሞት ለአሜሪካ” የሚል መፈክር ግን የላትም ብለዋል።
ነገር ግን ኢራን በዓላማዋ እና በአጥፊነት አቅሟ ‹‹50 ሰሜን ኮሪያዎችን›› እንደምትመጥን ገልጸዋል።
ኢራን የአሜሪካን እና የእስራኤልን ጥፋት እንደ ዋና ግብ ይዛ የተነሳች ሀገር መሆኗንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ለቴህራን ያላቸውን የጸና ድጋፍ በይፋ ገልጸዋል።
መሪው በሰጡት መግለጫ፤ እስራኤልን ከዓለም ካርታ ላይ ለማጥፋት ‹‹አንድ ሚሳኤል ብቻ በቂ ነው›› በማለት የፒዮንግያንግን የኒውክሌር አቅም ለዛቻ ተጠቅመውበታል።
አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እስራኤልን መምታት የሚያስችሉ የላቁ ሚሳኤሎችን ለኢራን ለማቅረብ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
የሰሜን ኮሪያ መግለጫ የወጣው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት “ኦፕሬሽን ኤፒክ ፉሪ” በተፋፋመበት እና የኢራኑ መሪ አያቶላ አሊ ኻሜኒ መገደላቸው በተረጋገጠበት ወቅት ነው።
በአሁኑ ወቅት ቻይና ለኢራን የላቁ ሚሳኤሎችን እያቀረበች እንደሆነ ይነገራል።
ቻይና ግን ለኢራን ወታደራዊ ድጋፍ እንደምታደርግ የሚገልጹ ሪፖርቶችን አስተባብላለች፡፡
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቀደም ሲል ‹‹ትልቁ›› ጦርነት ሊመጣ ይችላል ብለው የሰጡትን ማስጠንቀቂያ ይህ አዲስ አሰላለፍ ይበልጥ እያጠናከረው ይገኛል።
ይህ በኢራን፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና ሰሜን ኮሪያ መካከል እየተፈጠረ ያለው ወታደራዊ አሰላለፍ የቀጣናውን ግጭት ወደ ዓለም አቀፍ ጦርነት ሊቀይረው ይችላል የሚል ከፍተኛ ስጋት በዓለም አቀፍ የነዳጅ ገበያ እና በጂኦ-ፖለቲካዊ መረጋጋት ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል።
ሀና ሰይፉ
የካቲት 24/2018 ዓ.ም
