130ኛው የአድዋ ድል በዓል እየተከበረ ባለበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፣ ኢትዮጵያ የዓድዋን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት እና የኩራት መንፈስ አሁን ላሉባት የኢኮኖሚና የቴክኖሎጂ ፈተናዎች መፍቻ ልትጠቀምበት ይገባል ያሉት ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ናቸው።
በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘውና የአፍሪካን የዲጂታል ተስፋ በሚቃኘው የ’Elevate Africa’ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የሥራና ክህሎት ሚኒስተሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የአድዋ ድል የጀግንነት ብቻ ሳይሆን የቅንጅትና የጋራ ራዕይ ውጤት መሆኑን ያወሱ ሲሆን፣ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ለሀገራዊ እና አህጉራዊ ስኬት የሚያስፈልገው አገር ወዳድነትም፤ የተለያዩ ዕውቀቶችንና ክህሎቶችን በማቀናጀት ለጋራ ብልጽግና መቆም ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለችበት ደረጃ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጊዜያት ፍጹም የተለየና ወደ ተሻለ መዋቅራዊ ለውጥ የተሸጋገረችበት ነው ሲሉም አክለዋል።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በዚህ ሂደት ውስጥ ስልታዊ የሆኑ የፖሊሲ ለውጦችን እያደረገ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፣ በተለይም ወጣቶችን ለወደፊቱ የሥራ ገበያ ለማዘጋጀት የሚያስችል የብሔራዊ ቴክኒክና ሙያ ስትራቴጂ ተሻሽሎ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸዋል።
ይህም የቴክኒክና ሙያ ሥልጠናዎች የወጣቶች የመጀመሪያ ምርጫ እንዲሆኑ ለማድረግ ያለመ እንደሆነ አንስተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በውጭ ሀገራት ስራ የሚሰማሩ ዜጎች መብታቸውና ጥቅማቸው በአስተማማኝ ሁኔታ እንዲከበር የሚያስችል አዲስ አዋጅ መውጣቱ ለዜጎች ደህንነት የተሰጠውን ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በዲጂታል ለውጥ የታጀበ የአገልግሎት ኢኮኖሚ ለመገንባት በምታደርገው ጉዞ፣ በተለይ ወጣት የሰው ሃይል በከፍተኛ ደረጃ መኖሩን የገለጹት ወ/ሮ ሙፈሪያት፤ ሀገሪቱ በቁጥር ብቻ ሳይሆን በፖሊሲና በስትራቴጂም ለቀጣዩ የኢንዱስትሪ ማዕበል ዝግጁ በመሆኗ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ ጋር እንዲተባበሩ ጥሪ አቅርበዋል።
አዲስአለም አበበ
የካቲት 25/2018 ዓ.ም
