በኢትዮጵያ የሚገኙ የጤና ተቋማት አካል ጉዳተኞችን ባማከለ መልኩ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ጤና ሚኒስቴር አዳዲስ ስትራቴጂዎችንና ፖሊሲዎችን በማውጣት ላይ መሆኑ ገልጿል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶች ጤና ፕሮግራም አስተባባሪ ሲስተር ዘምዘም መሀመድ እንዳስታወቁት፤ በሀገሪቱ ካለው ጠቅላላ ህዝብ ውስጥ ከ18 እስከ 20 በመቶ የሚሆነው ማህበረሰብ የተለያየ የአካል ጉዳት ያለበት መሆኑን ተናግረዋል።
ሆኖም የጤና ተቋማት የህንጻ ዲዛይንና አሰራር ለእነዚህ የማህበረሰብ ክፍሎች ምቹ አይደለም ሲሉ ገልፀዋል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት ሚኒስቴሩ የጤና ተቋማት ቢያንስ 80 በመቶ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ መሆን አለባቸው የሚል ስትራቴጂ አስቀምጦ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም መሰረት አዳዲስ የሚገነቡትም ሆነ ነባር የጤና ተቋማት የዊልቸር መወጣጫ ፣ ለአካል ጉዳተኞች ምቹ የሆኑ መፀዳጃ ቤቶች ፣ እንዲሁም በወሊድ ክፍሎች አካል ጉዳተኛ እናቶችን ሊያስተናግዱ የሚችሉ አልጋዎች እንዲኖሯቸው እየተደረገ ስለመሆኑ ተነግሯል።
በተጨማሪም የጤና ባለሙያዎች የምልክት ቋንቋ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ላይ መሆኑን ኃላፊዋ ነግረዉናል።
ሊዲያ ደሳለኝ
የካቲት 25/2018 ዓ.ም
