መንፈሳዊ አገልግሎትን ከዘመናዊ የሕክምና ልማት ጋር ያጣመረው የመካነ ሕይወት ጮቤ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም፤ በኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ታሪክ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍትና ከሺህ በላይ አልጋዎችን የሚይዝ ግዙፍ የሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ሊያስጀምር መሆኑን ተገልጿል።
ዜጎች ለከፍተኛ ሕክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚያደርጉትን እንግልትና ወጪ ያስቀራል የተባለለት ይህ ፕሮጀክት፤ ገዳሙ ላለፉት 20 ዓመታት ሲያከናውናቸው የቆዩ የልማት ስራዎች ማሳረጊያ እንደሚሆን ተነግሮለታል።
በ1993 ዓ.ም የተመሰረተው የመካነ ሕይወት ጮቤ በዓታ ለማርያም አንድነት ገዳም፤ የሃይማኖት ተቋማት ለማህበረሰብ ልማት ያላቸውን ሚና በተግባር እያሳየ ይገኛልም ተብሏል።
ገዳሙ በዛሬው እለት በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጸው፤ አሁን ላይ ትኩረቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ አሻራ ያሳርፋል የተባለለትን ግዙፍ የሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ላይ አድርጓል።
የገዳሙ አበምኔት አባ ተክለሃይማኖት ገብረሕይወት እንደገለጹት፤ ይህ የሪፈራል ሆስፒታል በ60 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ላይ የሚያርፍ ሲሆን፣ 1 ሺህ 88 አልጋዎችን የመያዝ አቅም ይኖረዋል።
ሆስፒታሉ ተገንብቶ ሲጠናቀቅ ዜጎች ለከፍተኛ ህክምና ወደ ውጭ ሀገር የሚሄዱበትን ከፍተኛ ወጪና እንግልት ያስቀራል ተብሎ ታምኖበታል። የፕሮጀክቱ የመሰረት ድንጋይም ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ መቀመጡ አስታውሰዋል።
ገዳሙ ባለፉት 20 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ብቻ ሳይሆን በትምህርት፣ በመሠረተ ልማትና በግብርና ዘርፎች ሰፊ ስራዎችን ማከናወኑንም የገዳሙ አበምኔት ገልጸዋል።
እስካሁን ባለው ሂደትም ከ3 ሺህ በላይ ህፃናት ተጠቃሚ የሆኑበት ዘመናዊ ትምህርት ቤት መክፈቱ፣ ለነዋሪዎች የ300 ሺህ ሊትር የውሃ ማጠራቀሚያ መገንባቱና የ8 ኪሎ ሜትር የገጠር መንገድ ማስገንባቱ ተጠቅሷል።
ይህንን ግዙፍ የሪፈራል ሆስፒታል ግንባታ ዳር ለማድረስም በቀጣዩ የካቲት 29 ቀን 2018 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ታላቅ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ተዘጋጅቷል።
ገዳሙ በሀገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለዚህ ታሪካዊ ፕሮጀክት ስኬት አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ጥሪ አቅርቧል።
ልኡል ወልዴ
የካቲት 25/2018 ዓ.ም
