የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በመጋዘን ደረሰኝ አማካኝነት ወደ ሁለት ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር እንዲመቻች ማድረጉን ገለጸ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የአርሶ አደሮችን፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትን እና የአቀናባሪዎችን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማረጋገጥ እየተገበረ ያለው የመጋዘን ደረሰኝ ብድር አገልግሎት ሥርዓት ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታዉቋል።

እንደ ምርት ገበያው መግለጫ፤ አምራቾችና ተገበያዮች ምርታቸውን በምርት ገበያው መጋዘን በማስገባት የሚረከቡትን ደረሰኝ ብቻ እንደ ማስያዣ በመጠቀም፣ ከምርት ገበያው ጋር አጋርነት ካላቸው ባንኮች ብድር የሚያገኙበት አሠራር ውጤት እያመጣ ይገኛል ብሏል።

በዚህም መሠረት በ2017 በጀት ዓመት 3መቶ75 ሺሕ 892.77 ኩንታል ምርትን እንደ ማስያዣ በመጠቀም ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ብድር ማመቻቸት ተችሏል።

በተያዘው በጀት ዓመትም በተመሳሳይ 2መቶ40 ሺህ 809 ኩንታል የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በማስያዣነት በማቅረብ፤ ከ9መቶ14 ሚሊየን 2መቶ28 ሺህ ብር በላይ ብድር ለአምራቾችና ለድርጅቶች እንዲሰጥ መደረጉ ተገልጿል፡፡

በሌላ በኩል፤የቢራ ገብስ ወደ ዘመናዊ ግብይት ሥርዓት እንዲገባ መደረጉን ተከትሎ፤በ2018 ዓ.ም የምርት ዘመን ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ለሙ እና ቢልቢሎ ወረዳዎች የተመረተ 1 ሺህ 8መቶ79 ኩንታል የቢራ ገብስ በአዳማ ቅርንጫፍ ለመጀመሪያ ጊዜ መቀበሉን አስታዉቋል፡፡

የቢራ ገብስ ወደ ዘመናዊ የግብይት ሥርዓቱ መግባቱ አምራቾች በመጋዘን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ከመሆኑም በላይ፤በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ወደ ሀገር የሚገባውን የቢራ ግብዓት በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት ፋይዳው የጎላ መሆኑ ተጠቁሟል።

የዕቃ ማከማቻ ደረሰኝ ሥርዓትን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 372/1996 ተፈጻሚ ለማድረግ የሚያስችል ደንብ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በትላንትናው ዕለት መጽደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የመጋዘን ደረሰኝ የብድር አገልግሎት ሥርዓትን ይበልጥ በማጠናከር አርሶ አደሮች፣ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና አቀናባሪዎች የፋይናንስ ሥርዓቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አበክሮ እንደሚሠራ አስታውቋል።

የካቲት 25/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *