የኢራንን ከፍተኛ ሥልጣን የተቆጣጠሩት ሞጅታባ ኻሜኒ ሁኔታዎች ውስብሰብ ናቸው። ኢራን ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከእስራኤል ጋር ውጊያ ውስጥ ገብታለች።
ሥርዓቱ በቅርቡ አገዛዙን በመቃወም በመላ አገሪቱ የተካሄደው ሕዝባዊ አመጽ ካስከተለው ተጽዕኖ በቅጡ አላገገመም።
አዲሱ የበላይ መሪ ከአገሪቱ ልሂቃን ያላቸውን ድጋፍ በፍጥነት እያጠናከሩ ቢሄዱም፤ የቅቡልነት ጥያቄዎች ከፊታቸው ተደቅኗል።
ከብዙ የሃይማኖት አባቶች በተለየ ሞጅታባ በሃይማኖታዊ ሰዎች ዘንድ አያቶላህ በመባል አይጠሩም።
ሞጅታባ የኢራንን ሰፊ ስትራቴጂ ከመቅረጻቸው በፊት፤ አዲሱ መሪ በመጀመሪያ ራሳቸውን በእስላማዊ ሪፐብሊክ ውስብስብ የኃይል መዋቅር ውስጥ ማጽናት አለባቸው።
ይህ ደግሞ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ከዘለቀው ምስጢራዊነት ብቅ ማለት እና አዲስ በተሾሙ ወታደራዊ አዛዦች፣ በተፎካካሪ የፖለቲካ ቡድኖች እና አሁን ሊቀበሏቸው በማይችሉ የሃይማኖት መሪዎች ላይ ሥልጣን ማሳየት ማለት ነው።
እስላማዊ ሪፐብሊክ ከአራት አስርት ዓመታት በላይ ሲንቀሳቀስ የቆየው በፖለቲካ ቡድኖች መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንዲኖር በማድረግ እና ለተቋማት አነስተኛ ሥልጣን በመስጠት ነው።
ነገር ግን ሁል ጊዜ ወሳኝ የሆኑ ጉዳዮች ላይ የመጨረሻው ይሁንታን የሚሰጡት የበላይ መሪው ናቸው።
አሊ ኻሜኒ ከሞቱ በኋላ ያለው ሳምንት ስርዓቱ በአንድ ሰው ላይ ምን ያህል ጥገኛ እንደሆነ አሳይቷል።
የበላይ መሪው በሌለበት፣ የውሳኔ አሰጣጡ ቆሟል እና እርግጠኛ አለመሆን በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ሰፍኗል።
የሃይማኖት ሊቃውንቱ ሞጅታባን ለመሾም በፍጥነት መንቀሳቀሳቸውም ግልጽ የሆነ ምልክት ለመላክ ይመስላል።
በኢራን ምንም መሠረታዊ ነገር አልተለወጠም፤ ባለሥልጣናቱ በግል እንደሚናገሩት “ሕይወት በተለመደው መንገድ ቀጥሏል።”
ሆኖም አዲስ መሪን መቀበል ይፋ እንደማድረጉ ቀላል አይደለም።
መጋቢት 01/2018 ዓ.ም
