በዓለም ላይ ካለው የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦት ውስጥ በግምት 20 በመቶ የሚሆነው በመደበኛነት በሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ በኩል ያልፋል።
የአሜሪካ እና የእስራኤል ጥቃቶች በኢራን ላይ እየበረቱ በመሄዳቸውና ጦርነቱ የሚያበቃበት ምልክት እየታየ ባልሆነበት ሁኔታ፤ በመርከብ ትራፊክ እና በኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች የነዳጅ ዋጋ ዛሬ ማለዳ አንድ በርሜል ከ100 ዶላር በላይ እንዲያልፍ አድርገዋል።
ኢራን በዱባይ የባሕር ዳርቻ አቅራቢያ አንዲት የዕቃ ጫኝ መርከብ የመታች ሲሆን፤ በባሕሬን ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢያ እሳት እንዲነሳ አድርጋለች፤ እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ ትልቅ የነዳጅ ቦታ ላይ የድሮን ጥቃት ሰንዝራለች።
በተጨማሪም በፋርስ ባሕረ ሰላጤ በሚገኘው የባስራ ወደብ ላይ በደረሰ ጥቃት ምክንያት ኢራቅ በሁሉም የነዳጅ ማስተላለፊያ ተርሚናሎች ላይ ሥራ እንድታቆም ተገድዳለች።
አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት በመሰንዘር ጦርነቱን ከቀሰቀሱ ወዲህ፣ ቴህራን አጥቂዎቹ ጥቃታቸውን እንዲያቆሙ ግፊት ለማድረግ ሲባል በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጉዳት የማድረስ ዘመቻ ጀምራለች።
በክልሉ ባሉ የኃይል መሠረተ ልማቶች ላይ ጥቃት ከመሰንዘር በተጨማሪ፤ ኢራን ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ወደ ሕንድ ውቅያኖስ በሚወስደውና የአለማችን አንድ አምስተኛ ነዳጅ በሚጓጓዝበት ስልታዊ የሆርሙዝ የባሕር ሰርጥ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር አድርጋለች።
በባሕር ሰርጡ ውስጥ ያለው እንቅስቃሴ በመቆሙ የዓለም አቀፍ መለኪያ የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ዛሬ የ9 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በአንድ በርሜል ከ100 ዶላር በላይ ሆኗል፤ ይህም ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ከነበረው ዋጋ የ38 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 03/2018 ዓ.ም
