ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ እና የውሃ አስተዳደር አፍሪካን እያስተማረች ነው

የዛምቤዚ የውሃ ተፋሰስ ኮሚሽን (ZAMCOM) ከፍተኛ ልዑክ፣ የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ እና የውሃ አስተዳደር ተሞክሮ ለመቅሰም አዲስ አበባ ገብቷል።

ልዑኩ በዋናነት የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር እና የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች አስተዳደር ተሞክሮን ወደ ዛምቤዚ ተፋሰስ ሀገራት ለማሸጋገር ያለመ ውይይት ከውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ጋር አካሂዷል።

በስምንት የደቡባዊ አፍሪካ ሀገራት መካከል የሚፈሰው የዛምቤዚ ወንዝ አስተዳዳሪ የሆነው የዛምኮም (ZAMCOM) ልዑክ፤ በኢትዮጵያ እያደረገ በሚገኘው ጉብኝት የኢትዮጵያን ግዙፍ የአካባቢ ጥበቃ እና የውሃ መሰረተ-ልማት ስራዎችን ተመልክቷል።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ፤ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን የ86 በመቶ የውሃ ድርሻ በኃላፊነት ስሜት ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ጭምር በሚጠቅም መልኩ እያስተዳደረች መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ባለፉት ሰባት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር ከ48 ቢሊዮን በላይ ችግኞች መተከላቸውንና ይህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እንዲሁም የውሃ ደህንነትን ለማረጋገጥ ትልቅ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ለልዑኩ አስረድተዋል።

የዛምኮም (ZAMCOM) ዋና ጸሐፊ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ስራዎቿ በአፍሪካ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የአመራርነት ሚናዋን እያስመሰከረች መሆኑን ገልጸዋል።

የዛምቤዚ ተፋሰስ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ድርቅ እና የጎርፍ አደጋ እየተፈተነ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ጸሐፊው፤ የኢትዮጵያን የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ተሞክሮ ለዛምቤዚ ወንዝ ተፋሰስ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ ነው ብለዋል።

ልዑኩ በቆይታው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች የውሃ መሰረተ-ልማቶችንና በአዲስ አበባ የሚገኙ የአረንጓዴ ልማት ኮሪደሮችን እንደሚጎበኝ ይጠበቃል።

ይህ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም በአፍሪካ የልማት ባንክ ድጋፍ የሚተገበር ሲሆን፤ ዓላማውም በሀገራቱ መካከል ያለውን የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ትብብር ማጠናከርና የአየር ንብረት ለውጥን በጋራ መቋቋም መሆኑ ተገልጿል።

ልዑል ወልዴ

መጋቢት 07/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *