ትውልደ ኢትዮጵያ/ሆላንዳዊቷ የረጅም ርቀት ኮከብ ሲፈን ሀሰን ከ2026 የለንደን ማራቶን ውጪ መሆኗ ተሰምቷል፡፡
አትሌቷ ከስድስት ሳምንታት በፊት በጅምናዚየም ልምምድ ላይ ሳለች ያጋጠማት የጅማት ጉዳት ከዚህ ውድድር ውጪ እንዳደረጋት ታውቋል፡፡
የ33 ዓመቷ ሲፈን በኢንስታግራም ገጿ ላይ ባሰፈረችው ፅሁፍ “በዘንድሮው የለንደን ማራቶን አልሳተፍም። ይህ ውድድር ለእኔ ትልቅ ትርጉም ስላለው በጣም አዝኛለሁ፤ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የጅማት ጉዳቴ እንቅፋት ሆኖብኛል፣ እናም ለውድድሩ በሚፈለገው ከፍተኛ ብቃት ላይ አይደለሁም። በዚህ የለንደን ማራቶን መወዳደርን በጣም ነው የምወደው፤ የመጀመሪያውን ማራቶን ውድድሬን ያሸነፍኩበት እና ብዙ ልዩ ትዝታዎች ያሉኝ ቦታ ነው። ነገር ግን በዓለም ላይ ካሉ ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ማራቶኖች አንዱ በመሆኑ፣ በዚያ ደረጃ ለመወዳደር ፍጹም በሆነ ጤንነት ላይ መሆን ያስፈልጋል” ብላለች፡፡
መጀመሪያ ላይ ጉዳቱ ቀላል እንደሆነ በማሰብ ልምምዷን ቀጥላ ነበር፤ ነገር ግን ልምምዱ እየጠነከረ ሲሄድ ጉዳቱ ዳግም ስላገረሸባት እንዳይባባስባት በማሰብ ከውድድሩ ለመውጣት ወስናለች። ትኩረቷንም “በማገገም እና በረጅም ጊዜ ጤንነቷ” ላይ ለማድረግ መርጣለች።
“ልምምዴ እየገፋ ሲሄድ በምጠብቀው ደረጃ አንጻር መዘጋጀት እንደማልችል ግልጽ ሆነልኝ። ሰውነቴን ማዳመጥ እና በትክክል በማገገም ላይ ማተኮር አለብኝ። ወደፊት በለንደን በሚኖሩ ሌሎች በርካታ የውድድር አጋጣሚዎች ተመልሼ ለመሳተፍ እጓጓለሁ” ስትልም አክላለች፡፡
ይህቺ ድንቅ አትሌት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ማራቶን የተሸጋገረችው በ2023 በዚሁ የለንደን ማራቶን ነበር፡፡
በወቅቱም 2:18:33 በሆነ ጊዜ ማሸነፍ ችላለች፡፡ ከስድስት ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ደግሞ የቺካጎ ማራቶንን በ2:13:44 አሸንፋለች።
በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ የማራቶን ውድድርን ከማሸነፏም በላይ በ5,000 ሜትር እና በ10,000 ሜትር ውድድሮች ሜዳሊያዎችን ማግኘት ችላለች። ባለፈው ዓመት በለንደን ማራቶን 3ኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀች ሲሆን፤ የ2025 የሲድኒ ማራቶን አሸናፊም ነበረች።
በዘንድሮው የለንደን ማራቶን የአምና አሸናፊዋ ትዕግስት አሰፋ ክብሯን ለማስጠበቅ ትሮጣለች፡፡ ለአሸናፊነቱም ከፍተኛ ግምት ተሰጥቷታል፡፡
የ2024 አሸናፊዋ ኬንያዊቷ ፔሬስ ጄፕቺርቺር ሌላኛዋ ተጠባቂ አትሌት ናት።
ከሌሎች ዋነኛ ተፎካካሪዎች መካከል የ2021 የለንደን ማራቶን አሸናፊዋ ኬንያዊቷ ጆይሲሊን ጄፕኮስጌይ፣ የሁለት ጊዜ የኒው ዮርክ እና የሁለት ጊዜ የቦስተን ማራቶን አሸናፊዋ ሌላኛዋ ኬንያዊት ሄለን ኦቢሪ እና የኡራጓይ የመጀመሪያዋ የዓለም ሻምፒዮና የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ ጁሊያ ፓተርኔን ይገኙበታል።
ተጠባቂው የለንደን ማራቶን የፊታችን ሚያዝያ 18 ቀን (April 26) እንዲካሄድ ይካሄዳል።
ምስጋናው ታደሰ
መጋቢት 15/2018 ዓ.ም
