ቻይና የአሽከርካሪዎችን “ጫና ለመቀነስ” የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ቀነሰች

ቻይና በኢራን ጦርነት ምክንያት የኢነርጂ ወጪዎች እየጨመሩ ባለበት በዚህ ወቅት፤በአሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰውን “ጫና ለመቀነስ” በማሰብ አቅዳው የነበረውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ገድባለች።

ኢራን በዓለም ላይ ካሉ እጅግ ስራ የሚበዛባቸው የነዳጅ ማጓጓዣ መስመሮች አንዱ የሆነውን የሆርሙዝ ወሽመጥን የዘጋችበት ይህ ግጭት፤ የሀገር ውስጥ የቤንዚን ዋጋ ከግጭቱ መጀመሪያ አንስቶ በ20 በመቶ ገደማ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡

የሀገር ውስጥ የቤንዚን እና የናፍጣ ዋጋ መጀመሪያ ላይ በአንድ ቶን በቅደም ተከተል በ2ሺ2 መቶ 5 ዩዋን ወይንም 3 መቶ20 ዶላር እንዲሁም ደግሞ በ2ሺ1መቶ20 ዩዋን እንዲጨምር ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ከመንግስት ማስተካከያ በኋላ ጭማሪው ከማክሰኞ ጀምሮ ወደ 1ሺ1መቶ60 ዩዋን እና 1ሺ1መቶ15 ዩዋን ዝቅ እንዲል ተደርጓል።

በቻይና ውስጥ ከ300 ሚሊየን በላይ አሽከርካሪዎች በነዳጅ በሚሰሩ መኪኖች ላይ የሚደገፉ ሲሆን፤ የባህረ ሰላጤው ሀገራት ለሀገሪቱ ዋነኛ የነዳጅ ምንጭ ናቸው።

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በበርካታ የቻይና ከተሞች በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ረጅም የተሽከርካሪ ሰልፎች የታዩ ሲሆን፤አንዳንዶቹ ማደያዎች ነዳጅ ማለቁን የሚገልጽ ማስታወቂያ እስከ መለጠፍ ደርሰዋል።

ይህ የቅርብ ጊዜ የዋጋ ጭማሪ ቅናሽ ቢደረግበትም እንኳ በዘንድሮው ዓመት የተደረገው አምስተኛው እና ትልቁ ጭማሪ ሆኖ ተመዝግቧል።

ማክሰኞ ዕለት የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ በአንድ በርሜል 100 ዶላር በላይ ከፍ ያለ ሲሆን፤ይህም የሆነው በአሜሪካ እና በኢራን መካከል ሊኖር ስለሚችል ንግግር የተለያዩ መረጃዎች በወጡ ማግስት የዋጋ መውረድ ከታየ በኋላ ነው።

ቤጂንግ ባለፉት ዓመታት ዝቅተኛ የድፍድፍ ነዳጅ ዋጋን እና ከባህረ ሰላጤው ሀገራት የሚገኘውን የተትረፈረፈ አቅርቦት በመጠቀም በዓለም ላይ ካሉት ትልቁን የነዳጅ ክምችት መገንባቷን የሳክሶ ባንክ የሸቀጦች ስትራቴጂ ኃላፊ ኦሌ ሀንሰን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ ዓመት ጥር እና የካቲት ወራት ብቻ ቤጂንግ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር በ16 በመቶ ብልጫ ያለው ድፍድፍ ነዳጅ መግዛቷን የጉምሩክ አስተዳደሩ መረጃ ያሳያል።

በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባት ኢራን፤ ለቻይና ርካሽ ድፍድፍ ነዳጅ በማቅረብ ቁልፍ ተዋናይ ስትሆን፣ ቤጂንግ ከኢራን የነዳጅ ኤክስፖርት ውስጥ ከ80 በመቶ በላይ የምትገዛ መሆኗን መረጃዎች ይጠቁማሉ።

ሀንሰን እንዳሉት ከሆነ ቻይና ወደ 900 ሚሊየን በርሜል የሚጠጋ ክምችት ያላት ሲሆን፤ይህም ለሦስት ወራት የሚጠጋ ፍጆታን ይሸፍናል።

በቻይና የመንግስት መገናኛ ብዙኃን የተጠቀሰው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ደግሞ የቻይና የቤንዚን ክምችት 1.4 ቢሊየን በርሜል ይደርሳል ይላል።

ቻይና የነዳጅ ክምችት ቢኖራትም የአጭር ጊዜ አቅርቦቷን ለመቆጣጠር ጥንቃቄ እያደረገች ነው። የሀገር ውስጥ ዋጋን ለመቆጣጠር ሲባል የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካዎች ለጊዜው ነዳጅ ወደ ውጭ መላክ እንዲያቆሙ ታዘዋል።

የቻይና ግዛት ፕላነር በሰጠው መግለጫ፤ “ያልተለመደውን የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተጽዕኖ ለመቀነስ እና የኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማረጋገጥ ጊዜያዊ የቁጥጥር እርምጃዎች ተወስደዋል” ብሏል።

ሌሎች የእስያ ሀገራትም እየናረ የመጣውን የኢነርጂ ዋጋ ለመቋቋም የተለያዩ የቁጠባ እርምጃዎችን እየወሰዱ ይገኛሉ፡፡

ሀና ሰይፉ

መጋቢት 15/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *