በሚቀጥለው ወር በአውሮፓ የኃይል እጥረት ሊከሰት እንደሚችል የሼል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተናገሩ

ሀገራት የኃይል ዋስትና ሳይኖራቸው ብሔራዊ ደህንነት ሊኖራቸው አይችልም ያሉት ዋኤል ሳዋን፥ሼል መንግስታት የኃይል ቀውሱን እንዲወጡ ለማገዝ በክምችት እና በግዢ ረገድ አብሮ ለመስራት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

አሁን አራተኛ ሳምንቱ ላይ የሚገኘው የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት አስቀድሞ የአውሮፕላን ነዳጅ አቅርቦት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን፤ ቀጥሎም በዲዝል ላይ፣ ከዚያም በሰሜን ንፍቀ ክበብ የበጋው ወቅት ሲጀመር በቤንዚን ላይ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ሳዋን ተናግረዋል።

ጦርነቱ ዋና ዋና የኃይል መሰረተ ልማቶችን የጎዳ ሲሆን፥በዓለም አቀፍ ደረጃ 20 በመቶ የሚሆነው የነዳጅ እና የፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ ዝውውር የሚያልፍበትን የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከሞላ ጎደል እንዲቆም አድርጓል።

አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የከፈቱት ጦርነት ወዴት ያመራል የሚለው ጉዳይ ግልጽ ባለመሆኑ፤የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ ዋጋ ተመልሶ በአንድ በርሜል ከ100 ዶላር በላይ ሆኗል።

ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፤ኢራን “ሙሉ በሙሉ ተሸንፋለች፤ዋሽንግተንም “ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ከሚያወሩ” የኢራን መሪዎች ጋር ድርድር እያደረገች ነዉ ብለዉ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ቴህራን ከአሜሪካ ጋር ግንኙነት አድርጌያለሁ የሚሉትን መረጃዎች ቀደም ሲል ውድቅ ያደረገች ሲሆን፤ይህንን መረጃ የኃይል ዋጋን እና የገበያ ሁኔታን ለመቆጣጠር የሚደረግ ሙከራ ነው ስትል ጠርታዋለች።

ቅዳሜና እሁድ ግጭቱ ሊባባስ ይችላል የሚለው ስጋት የዓለም የነዳጅ ዋጋ መለኪያ የሆነው የብሬንት ዋጋ 1መቶ13 ዶላር እንዲደርስ አድርጎ ነበር።

ትራምፕ በዋሽንግተን እና በቴህራን መካከል ግጭቱን ለመፍታት ውጤታማ ንግግሮች እየተደረጉ መሆኑን በመጥቀስ፤ አሜሪካ በኢራን የኢነርጂ መሰረተ ልማቶች ላይ የምታደርገውን ጥቃት ለአምስት ቀናት እንደምታራዝም ከተናገሩ በኋላ ሰኞ ዕለት የነዳጅ ዋጋ ቀንሶ ነበር።

ማክሰኞ ግን ስለ ንግግሮቹ ውጤታማነት ጥርጣሬ በመፈጠሩ ዋጋው ተመልሶ ወደ 103 ዶላር ከፍ ብሏል።

በዓለም ዙሪያ ያሉ አገራት የኃይል ዋጋ መጨመርን እና የአቅርቦት መስተጓጎልን ተፅዕኖ ለመቀነስ ጥረት አድርገዋል።

አሜሪካ በ2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ባደረገችዉ ወረራ ምክንያት በሩሲያ ላይ ጥላው የነበረውን ማዕቀብ ለጊዜው ያነሳች ሲሆን፤በባህር ላይ ባለው የኢራን ነዳጅ ላይ የነበረውን ማዕቀብም አቅልላለች ሲል የዘገበዉ ሮይተርስ ነዉ።

እስከዳር ግርማ

መጋቢት 16/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *