ይህ ብይን አንድ የአሜሪካ ግዛት የማህበራዊ ሚዲያ ግዙፉን ኩባንያ በህፃናት ደህንነት ጉዳይ ላይ በተሳካ ሁኔታ የከሰሰበት የመጀመሪያው አጋጣሚ ነው።
በአሜሪካ የሚገኝ የዳኞች ቡድን ግዙፉ የማህበራዊ ሚዲያ ኩባንያ ሜታ፥ የህፃናትን የአእምሮ ጤና በመጉዳቱ እና ለጾታዊ ብዝበዛ ተጋላጭ በማድረጉ 3መቶ75 ሚሊየን ዶላር እንዲከፍል ወስኗል።
በኒው ሜክሲኮ የሚገኙ ዳኞች ይህንን ብይን ያስተላለፉት ማክሰኞ ዕለት ሲሆን፥ ይህም የክልሉ ባለስልጣናት ግዙፉ ኩባንያ ለአካለ መጠን ያልደረሱ ልጆችን መጠበቅ አልቻለም ብለው ለስድስት ሳምንታት ሲከሱት ከቆዩ በኋላ ነው።
የኢንስታግራም፣ የፌስቡክ እና የዋትስአፕ እናት ኩባንያ የሆነው ሜታ፥ መድረኮቹ በወጣቶች የአዕምሮ ጤና ላይ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምክንያት በርካታ ክሶች እየቀረቡበት ይገኛል።
ዳኞቹ፥ሜታ “ከደህንነት ይልቅ ለትርፍ ቅድሚያ ሰጥቷል” የሚለውን የክልሉን አቃቤ ህግ መከራከሪያ ተቀብለዋል።
ዳኞቹ የኩባንያው ሰራተኞች የነበሩ ምስክሮችን ጨምሮ የ40 ሰዎችን ምስክርነት የሰሙ ሲሆን፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰነዶችን፣ ሪፖርቶችን እና ኢሜይሎችን መርምረዋል።
የሜታ ቃል አቀባይ በሰጡት መግለጫ፥ “በውሳኔው ላይ ቅሬታ አለን፤ ይግባኝም እንጠይቃለን” ብለዋል።
የኒው ሜክሲኮ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ራውል ቶሬዝ፥ ሜታን እና ዋና ስራ አስፈጻሚውን ማርክ ዙከርበርግን ወደ ፍርድ ቤት ያቀረቡት በ2023 ሲሆን፥ ይህም መርማሪዎች ዕድሜያቸው ከ14 ዓመት በታች የሆኑ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ተጠቃሚ በመምሰል ባደረጉት ሚስጥራዊ ምርመራ ነው።
ቶሬዝ በሰጡት መግለጫ ውሳኔው፥ሜታ ለህፃናት ደህንነት ሳይሆን ለትርፍ በመጨነቁ ምክንያት “ዋጋ ለከፈሉ” ህፃናት እና ቤተሰቦች ሁሉ ታሪካዊ ድል ነው ብለዋል።
ዳኞቹ ሜታ እንዲከፍል የወሰኑት ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ለማንኛውም የቴክኖሎጂ ኩባንያ የበላይ አመራሮች “የትኛውም” ኩባንያ ከህግ በላይ እንዳልሆነ ግልጽ መልእክት የሚያስተላልፍ ነው ሲሉም አክለዋል።
በኒው ሜክሲኮ በሜታ ላይ የተጀመረው የክስ ሂደት በሚቀጥለው ግንቦት ወር የሚቀጥል ሲሆን፥ በወቅቱም ዳኛው ኩባንያው ተጨማሪ ቅጣቶችን እንዲከፍል እና በአሰራሩ ላይ ግልጽ ለውጦችን እንዲያደርግ ትእዛዝ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
እስከዳር ግርማ
መጋቢት 16/2018 ዓ.ም
