አዲስ አበባን የዓለም አቀፍ ቢዝነስ መሪዎች ማዕከል የሚያደርጋት 4ኛው የ‹‹ኢንቨስት በኢትዮጵያ›› ፎረም ተከፈተ

መጋቢት 17 ቀን 2018 ዓ.ም ‹‹ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ዝግጁ ናት›› በሚል መሪ ቃል በርካታ ባለሀብቶችን የሳበ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ ተጀምሯል፡፡

በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከገንዘብ ሚኒስቴር እና ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር የተዘጋጀው ይህ ጉባኤ፤በሀገሪቱ ያሉ ያልተነኩ የኢንቨስትመንት አማራጮችን ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ያለመ ነው።

ፎረሙ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን፤ በቆይታው የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ቁልፍ ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚመክር ይጠበቃል፡፡

በጉባኤው ላይ ከ800 በላይ የሚሆኑ ዓለም አቀፍ ባለሀብቶች፣ ከፍተኛ የፖሊሲ አውጪዎች እና የንግድ መሪዎች ተገኝተዋል።

መድረኩ በዋናነት በግብርና እና ማኑፋክቸሪንግ፣በኢነርጂ እና ማዕድን፣በአይሲቲ እና ቱሪዝም እንዲሁም ዲጂታል ኢኮኖሚን መገንባት እና የቱሪስት መዳረሻዎችን ማልማት በሚሉ ስትራቴጂካዊ ዘርፎች ላይ ያተኩራል ተብሏል፡፡

ፎረሙ ከመደበኛ ንግግሮች ባለፈ ተግባራዊ የንግድ ትስስሮችን ለመፍጠር አልሟል፡፡

በመሆኑም በሀገር ውስጥና በውጭ ባለሀብቶች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር የጋራ ኩባንያዎችን ማቋቋም፣በኢንቨስትመንት ዙሪያ ያሉ ማነቆዎችን ለመፍታትና ምቹ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት የሚረዱ ምክክሮችን ማድረግ እንዲሁም የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አቅም በተግባር የሚያሳዩ ትዕይንቶች ማጉላት የጉባኤው ዋና አላማ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በጉባኤው መክፈቻ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፤ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ለአልሚዎች በሯ ክፍት ነው ብለዋል::

ይህ ጉባኤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ያላትን የኢኮኖሚ መሪነት ሚና ለማጠናከርና አዳዲስ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ ትልቅ ዕድል ይዞ እንደሚመጣ ይጠበቃል።

ሀና ሰይፉ

መጋቢት 17/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *