በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን በክልሉ ተገኝቶ ማድረግ እንደማይችል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አረጋገጠ

ሆኖም በክልሉ ተወካዮች ሂደቱን በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታዉቋል።

ከዚህ ቀደም በክልሉ ተገኝቶ የአጀንዳ ማሰባሰብ እንዲሁም የተሳታፊዎች ልየታ ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር እየሞከረ እንደሚገኝ ተነግሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰቡም እና የተሳታፊዎች ልየታ በተወካዮች በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ተወስኗል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በዛሬዉ ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጠዉ ጋዜጣዊ መግለጫ በክልሉ ዉስጥ ተገኝቶ ሂደቱን ማስጀመር እንደማይችል አረጋግጧል፡፡

የኮሚሽኑ ኮሚሽነር በሰጡት መግለጫ ሂደቱ በአዲስ አበባ ከመጋቢት 23 እስከ 25፤ በመቀሌ እና በአዲስ አበባ በሚገኙ ከክልሉ ተወላጆች እና ተወካይ ተሳታፊዎች፣የሲቪል ማህበራት እና ሌሎች በተገኙበት እንደሚካሄድ ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ ከዚህ ዉሳኔ አስቀድሞ በትግራይ ክልል በአምስት የዞን ከተሞች ላይ ሂደቱን ለማስጀመር ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ከስምምነት ቢደርስም ምክንያቱ ባልታወቀ ምክንያት ፍቃድ አለማግኘታቸዉን አስታዉሰዋል።

በመቀሌ እና አዲስ አበባ ውይይቶች ሳይቋረጡ ሲደረጉ እንደነበር ኮምሽኑ ያስታወቀ ሲሆን፤በቀጥታ ማግኘት ያልቻለዉ የወረዳ ተሳታፊዎችን እንደሆነ ተገልጿል።

ኮሚሽነር መስፍን፤ እስከ ትናንት ድረስ ከ70 በላይ ከሚሆኑ የትግራይ ተወላጆች ጋር ሆኖ ያሏቸዉን ጥያቄዎች እየተቀበለ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህ በአዲስ አበባ በሚደረገዉ የምክክሩ ሂደት ከ 4 መቶ በላይ ተሳታፊ እንደሚገኝ የተገመተ ሲሆን፤ የትራንስፖርት ሁኔታን ለማመቻቸት ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ትብብር እንደሚደረግ በመግለጫዉ ተጠቅሷል።

ኮሚሽነር መስፍን አርአያ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮምሽን 93 በመቶ ስራዉን አጠናቋል፤ የቀረዉ የትግራይ ክልል 7 በመቶ ሂደት ግን በትኩረት እየተሰራበት ይቀጥላል ብለዋል።

በአዲስ አበባ በሚደረገዉ የክልሉ ተወካዮች የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አስፈላጊ ጥረት ተደርጎ እንደሚካሄድ ለዚህም ለተሳታፊዎች ኮምሽኑ ጥሪዉን አቅርቧል።

ኮሚሽኑ የአራት አመታት የስራ ክንዉን አፈፃፀሙን ለእንደራሴዎቹ ምክር ቤት አባላት ገለፃ ባደረገበት ወቅት በትግራይ ክልል በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተቀመጡ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች በክልሉ ለማካሄድ ለታሰበዉ የተሳታፊ ልየታ እና የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት አስቻይ ሁኔታ እንዳይፈጠር ስለማድረጉ ተገልፆ ነበር።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የስራ ዘመን ከየካቲት 15 ጀምሮ የተቆጠረ የስምንት ወራት የስራ ዘመን ጊዜ ተጨምሮለት እንደነበር ይታወሳል።

ቁምነገር አየለ

መጋቢት 18/2018 ዓ.ም

FacebooktwitterredditpinterestlinkedinmailFacebooktwitterredditpinterestlinkedinmail

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *